የአውስትራልያ የወፎች ዝማሬ አልበም የሙዚቃ ክብረ ወስን ሰበረ
53 ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡ ወፎች የተሳተፉበት አልበም ቅንብር 30 ዓመት ፈጅቷል ነው የተባለው
አልበሙ እንደ ማሪያህ ኬሪ የመሳሰሉ ሥመ ጥር ሙዚቀኞችን በልጦ በደረጃ ሰንጠረዡ ማማ ላይ መውጣቱ አነጋጋሪ ሆኗል
በአውስትራሊያ የወፎች ዝማሬ በሙዚቃ ደረጃ ዝርዝር (ቻርት) ላይ ክብረ ወሰን መስበሩ ተሰማ።
በ“በርድዝ ላይፍ አውስትራልያ” የተሰኘ ድርጅት አማካኝነት በታህሳስ 3 ተቀርጾ የቀረበው የወፎች ዝማሬ፤ በአውስራሊያ የሙዚቃ ደረጃ (አሪያ ሙዚክ ቻርት) ከአምስቱ ከፍተኛ ተወዳጅ ሙዚቃዎች አንዱ ለመሆን በቅቷልም ነው የተባለው።
የመጥፋት ዜማ ወይም 'ሶንግስ ኦፍ ዲሳፒራንስ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሙሉ በሙሉ የመጥፋት አደጋ ላይ ከሚገኙ ወፎች ዜማ፤ እጅግ ስመጥር ዘፋኞችን በልጦ በደረጃ ሰንጠረዡ ማማ ላይ ለመውጣት መቻሉንም አነጋጋሪ ሆኗል ይለናል የሲ.ኤን.ኤን ዘገባ።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ካናዳዊ ዘ ዊክኢንድ (አቤል ተስፋዬ)፣ የስዊድኖቹ ዝነኛ የሙዚቃ ቡድን (አባ)፣ የገና በዓል (ክሪስማስ) ተወዳጅ ዘፋኞች ማይክል በብል እና ማሪያህ ኬሪ የወፎቹ ዝማሬ ከሙዚቃ ደረጃ ዝርዝሩ ውስጥ ከበለጣቸው ሥመ ጥር ዓለም አቀፍ አቀንቃኞች መካከል ናቸው።
የዱር ወፎች ዝማሬ አቀናባሪ ዳቪድ ስቴዋርት “53 ዝርያቸው ለመጥፋት የተቃረቡ ወፎች የተሳተፉበት አልበም ቅንብር ለማሰናዳት 30 ዓመት ፈጅቷል” ብሏል።
አልበሙ በማኅበራዊ ሚዲያ ለሕዝብ ከቀረበ ሳምንት ብቻ ቢሆነውም፤ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል።
ይህ የአእዋፋቱ ዝማሬ በአውስራሊያ ታሪክ ብቻም ሳይሆን በዓለም ታሪክ አዲስ የሙዚቃ ክብረ ወሰን ለመያዝ እንደቻለ ተነግሯል።
በአውስትራሊያ ከሚገኙ 6 ወፎች አንዱ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል። ዋናው ምክንያት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ነው። የወፎቹ አልበም የተቀናበረውም ይህን ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ተብሏል።