ለጨዋታ ሜዳ ሲገባ ደጋዎች እንደሚቀልዱበትና አጨዋወቱን ካዩ በኋላ ግን እሱን እንደሚደግፉም ይገልጻል
“እኔ፣ እናቴ እና ወንድሜ አብረን ነው የምንኖረው፤ ሶስታችንም ቁመታችን በጣም አጭር ነው፤ እናታችን ያለማንም እርዳታ ብቻዋን ነው ያሳደገችን” ይላል ባለታሪኩ ጀስቲን።
ጀስቲን ስለ እናቱ ሲናገርም፤ “ሁሌም ጠንካራ እንድንሆን ታበረታታናለች፤ አንዳንዴ ራሴን ለማጥፋጥት እፈልጋለሁ፤ እናቴ ግን አንተ ልዩ ሰው ነህ፣ እናትህ እና ወንድምህ ይወዱሃል እያለች ታጽናናኛለች” ይላል።
“እናቴ የቤታችን የጀርባ አጥንት ነች” የሚለው ጀስቲን፤ “ሰዎች በጣም አያፈጠጡብን ተቸገርን ብለን ስንነግራት እናንተም መልሳችሁ አፍጥጡባቸው ትለናልች፤ ከሰዎች ጋር ስጣላም አትናደድብኝም፤ ይልቁንም ራስህን ለመከላከል ነው ያደረከው፤ ቀጣይ የሚያስቸግር ካለም ማድረግ ትችላለህ እያለች ታበረታታኛለች” ሲልም ይናገራል።
ቅርጫት ኳስ እንዲጫወቱም እናቱ እንዳበረታታችው የሚናገረው ጀስቲን፤ ቅርጫት ኳስ መጫወትን ታላቅ ወንድሙ ቀድሞ እንደጀመረውም ተናግሯል።
ቅርጫት ኳስ መጫወት የጀመረውም በሰፈሩ ባለ ማእከል ውስጥ እንደሆነ የሚናገረው ጀስቲን፤ እዛ በነበረው ቆይታም የቁመት ማጠር የአካል ጉዳት ሳይሆን በአግባብ የመጠቀም ጉዳይ መሆኑን እንደተረዳም ይናገራል።
ቁመቱ አጭር የሆነ ሰው ኳስን በመሬት ላይ ማንጠር የግድ ይለዋል ያለው ጀስቲን፤ “እኔን መግጠም የሚፈልግ ሰው ዝቅ ብዬ እገኛለሁ፤እዛ መጥቶ ፈልገኝ፤ የእኔ ዓለም እዚህ ነው” ብሏል።
ሰፈር ውስጥ በነበረው የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ላይ ሁሉም ሰዎች ያከብሩት እንደነበረ እና ስለእሱ መጥፎ ነገር የሚያወራ ሰው እንደሌለ የሚናገረው ጀስቲን፤ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ ለጨዋታ ወደ ሌሎች ሜዳዎች ሲሄድ ከደጋፊዎች ጸያፍ ቃል ይደርሱት እንደነበረ ይናገራል።
“በዚህ ወቅት ከእኔ ጋር የሚጫወቱ የቡድን አባላት እና ጓደኞቼ እኔን ለመጠበቅ እና ለማበረታታት ይጥራሉ፤ ግን ከ300 በላይ ሰዎች በቁመትህ ምክንያት ሲቀልዱብህ ምንም ለማድረግ አቅም አይኖርህም” ይላል።
“ወደ ሜዳ መግባት በጣም ነው የምጠላው፤ ሜዳ ውስጥ ያሉ ደጋፊዎች ምን ያክል ሰው እንደሚያስከፉ ማንኛውንም አጭር ሰው ብትጠይቅ ሊነግርህ ይችላል” ብሏል ጀስቲን።
“ሜዳ ውስጥ ገብቼ መጫወት ስጀምር ግን አጨዋወቴን እያዩ ለኔ ድጋፍ መስጠት ይጀምራሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ እንደእኔ አይነት ሰው ቅርጫት ኳስ ሲጫወት አይተው ስለማያቁ ነው” ብሏል።