ሱዳናውያን የፖለቲካ ስምምነት ማእቀፍ ነገ ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል
ስምምነቱን የሀገሪቱ የሉአላዊ ምክር ቤት እና የነጻነትና ለውጥ ጥምረት ይፈራረሙታል
ስምምነቱ ወታደሩ የተቆጣጠረውን ስልጣን ለመጋራት እና ተቋማትን በሲቪል አስተዳደር ውስጥ ለማስገባት ያግዛል ነው ተብሏል
ሱዳናውያን በነገው እለት የሚፈረመውን የፖለቲካ ስምምነት እየተጠባበቁ ነው።
የሀገሪቱ የሉአላዊ ምክር ቤት እና የነጻነትና ለውጥ ጥምረት ስምምነቱን ለመፈራረም ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የፖፑላር ኮንግርስ ፓርቲ፣ ዴሞክራቱክ ዩኒየኒስት ፓርቲ እና የሱዳን አብዮታዊ ግንባርም በስምምነቱ ይካተታሉ ተብሏል።
የፓርቲዎቹ አመራሮች ባለፈው አርብ ከሱዳን የሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን እና ከፈጥኖ ድራሽ ሃይሉ መሪ ሌተናል ጀነራል ሞሃምድ ሃምዳን ዳጋሎ ጋር ነገ ስለሚፈረመው ስምምነት መክረዋል።
ሲቪል የሽግግር መንግስትን ለማቋቋም መሰረት ይጥላል የተባለው ስምምነት ወታደራዊ ሃይሉ የተቆጣጠረውን ስልጣን እንዲያጋራ ያደርገዋል።
ተቋማትንም ሙሉ በሙሉ በሲቪል አስተዳደር ውስጥ ለማስገባት ያግዛል ነው የተባለው።
በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር ሀስን አልበሽር የሚመራው የፓርቲዎች ጥምረት ግን የስምምነቱን መፈረም እየተቃወመ ነው፤ የካርቱምን አደባባዮች በአምጽ እንደሚያጥለቀልቅም ዝቷል።
የሱዳን ኮንግርንስ ፓርቲም የሱዳንን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የመንግስታቱ ድርጅትን ሚና መቃወሙ ነው የተነገረው።
የሱዳን የባለሙያዎች ማህበር፣ የኮሚዩኒስት ፓርቲ እና አነስተኛ ተቀባይነት ያላቸው ፓርቲዎች እያነሱት ያለው ተቃውሞ ግን ውሃ የሚያነሳ አይደለም የሚሉ ትችቶች እየተሰነዘሩ ነው።
የስምምነት ማዕቀፉ ካለፈው አመት ሀምሌ ወር ጀምሮ በወታደራዊ ሃይሉና በነጻነትና ለውጥ ጥምረት መካከል ድርድር ሲደረግበት ቆይቷል።
ሂደቱንም አሜሪካን ያካተቱ አራት ኮሚቴዎች ሲከታተሉት የቆዩ ሲሆን፥ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ብሪታንያ ድጋፍ ማድረጋቸው ተመላክቷል።
የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረትና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት ኢጋድ የካርቱምን ፖለቲካዊ ትኩሳት ማብረድ ያስችላል የተባለው ስምምነት እንዲደረስ ማገዛቸው ነው የተገለጸው።
የታሰሩ አባላቶቻችን ሳይፈቱ የስምምነት ማዕቀፉን አንፈርምም፤ በምክክሩም አልተሳተፍንም የሚሉ የሱዳን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን ቢያንስ በነገው እለት እንዳይፈረም ጫና እያደረጉ ነው።
ከስምምነት ማዕቀፉ መፈረም በኋላ ፈራሚዎቹ ወገኖች አራት ሰነዶችን በጋራ እንዲያዘጋጁ ይደረጋል።
ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የሽግግር ፍትህ መዘርጋት፣ የቀድሞውን የአል በሽር ስርአት ማፈራርስ፣ የጁባውን የሰላም ስምምነት መገምገም እና የጸጥታውን ዘርፍ ሪፎርም ማድረግን የተመለከቱ ሰነዶች ይዘጋጃሉ።
እነዚህ ሰነዶች በአንድ ወር ውስጥ ከተጠናቀቁ በኋላም ፓርቲዎች ፊርማቸውን አሳርፈውበት ዘላjቂ ሰላምን ወደሚያመጡ ስራዎች ይገባሉ ነው የተባለው።
ሱዳን ከጥቅምት 2021ዱ የመፈንቅለ መንግስት በኋላ የሲቪል አስተዳደር ይመለስ በሚሉ ሰልፈኞች አደባባዮቹ እንደተሞሉ ናቸው።
aXA6IDE4LjE5MC4yMTcuMTM0IA== ejasoft island