የሱዳን መንግሥት እና ታጣቂ አማጺያን የመጨረሻ የሰላም ስምምነት ከ2 ቀናት በኋላ ይፈራረማሉ
ባለፉት 17 ዓመታት በአማጺያን እና በመንግስት መካከል በተደረገ ዉጊያ በ100 ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ረግፏል
መንግስትና አማጺያን ከወር በፊት የመጀመሪያ ዙር የሰላም ስምምነት በጁባ ተፈራርመዋል
የሱዳን መንግሥት እና ታጣቂ አማጺያን የመጨረሻ የሰላም ስምምነት ከ2 ቀናት በኋላ ይፈራረማሉ
የሱዳን መንግሥት እና ታጣቂ አማጺያን በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የመጨረሻ የሰላም ስምምነት መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚፈረም የሱዳን ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄነራል መሐመድ ሀምዳን ደጋሎ ለዚሁ ጉዳይ ዛሬ ወደ ጁባ አቅንተዋል፡፡
መንግሥትና አማጺያኑ ከወር በፊት በዚያው በጁባ የመጀመሪያ ዙር የሰላም ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በጥቂት ቀናት ልዩነት በሱዳን መንግስት በኩል የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጭ ንቅናቄ የሰሜኑ ክንፍ (SPLM-N) ደግሞ በተናጥል በአዲስ አበባ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሃምዶክ በጁባ በተደረገው ድርድር ለመስማማት ፈቃደኛ ካልሆነው የሱዳን ሕዝባዊ ነፃነት ንቅናቄ-ሰሜን (ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም./SPLM-N) አማጺ ቡድን ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ ስምምነት መፈራረማቸውን የሁለቱ ወገኖች ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡
የሱዳን የረጅም ጊዜ መሪ ኦማር አልበሽር ፣ ለወራት የዘለቀውን ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ፣ እ.አ.ኤ. ሚያዚያ 2019 ከስልጣን ሲወገዱ ወደ ኃላፊነት የመጣው የሱዳን የሽግግር መንግስት ከዓማጺያን ቡድኖች ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረስን ቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ስምምነቱ በዋነኝነት በፀጥታ ፣ በመሬት ባለቤትነት ፣ በሽግግር ፍትህ ፣ በስልጣን ማጋራት እና በጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የተሰደዱ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በተጨማሪም የአማጺ ኃይሎችን ማፍረስ እና ተዋጊዎቻቸውን ወደ ብሔራዊ ጦር ስለማቀላቀልም ይመለከታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2003 አማጺያን መሳሪያ ካነገቡ በኋላ በዳርፉር ብቻ በተካሄደው ውጊያ 300,000 ያህል ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡