ኢትዮጵያ ለሱዳን የላከችውን የሰብዓዊ ድጋፍ የያዘው አውሮፕላን ካርቱም ደርሷል
አቶ ገዱ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት መሪ አል ቡርሃን ጋር ተገናኝተዋል
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራ ልዑክ ድጋፉን ይዞ ዛሬ ከሰዓት ካርቱም ገብቷል
ኢትዮጵያ ለሱዳን የላከችውን የሰብዓዊ ድጋፍ የያዘው አውሮፕላን ካርቱም ደርሷል
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ይዞት የሄደው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ አውሮፕላን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ካርቱም አየር ማረፊያ ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር እስማኤል ቀመረዲን አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አደም መሀመድ እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ካርቱም ያቀናው ልዑክ አካል ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቀደም ሲል ድጋፍ ለማድረግ ኢትዮጵያ የገባችውን ቃል ወደ ተግባር ለመቀየር ወደ ሱዳን እንደሄዱ ገልፀው ሀገራቸው ከሱዳን መንግስት እና ህዝብ ጋር ያለውን አጋርነት በማረጋገጥ ከሱዳን ጎን ለመቆም ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኗን አስረድተዋል፡፡
ምንም እንኳን እንደሱዳን ሁሉ ኢትዮጵያም ባለፉት ሁለት ወራት የጎርፍ አደጋ ቢደርስባትም ለሱዳን ህዝብና መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያለውን ድጋፍ እና አጋርነት ለመግለጽ ወደ ካርቱም መሄዳቸውንም አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡
ኦማር ኢስማኤል ቀማርዲን በበኩላቸው በቀጣይነትም የበለጠ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንን እንዳመሰገኑ የሱዳን ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
እርዳታው 60 ቶን ምግብ እና መድሃኒት ያካተተ መሆኑም ነው በዘገባው የተጠቀሰው፡፡
ሱዳን በክረምቱ ከፍተኛ ዝናብ እና በዓባይ ወንዝ ሙላት በደረሰባት የጎርፍ አደጋ ከ100 በላይ ሰዎች የሞቱባት ሲሆን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ መፈናቀሉ ይታወሳል፡፡
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ መወያየታቸውንም ገልጸዋል፡፡