ዛሬ ንጋት ላይ ሰመራን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጨረቃ በከፊል ተጋርዳ መታየቷ ተገለጸ
ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ መሬት በጸሃይና ጨረቃ መካከል ስትሆን የሚከሰት ነው
በሰመራ የጨረቃ ግርዶሽ ትእይንት እንደነበር የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታውቋል
ዛሬ ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ/ም ንጋት 11፡00 ላይ ሰመራን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጨረቃ በከፊል ተጋርዳ መታየቷ ተገለጸ፡፡
ከፊል የጨረቃ ግርዶሹ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የደቡብ አሜሪካ፣ አውሮፓ ሃገራት እና በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች መከሰቱን እንደነበር የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገልጿል።
ኢንስቲትዩቱ ከሠመራ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የጨረቃ ግርዶሽ ትእይንቱን ለዩኒቨርሲቲዉ እና ለአካባቢው ማህበረሰብ ሲያሳይ እንደነበርም ነው ኢንስቲትዩቱ የገለጸው፡፡
ከፊል የጨረቃ ግርዶሹ በአፋር አካባቢ ከንጋቱ 11 ሰአት ጀምሮ በቀላሉ በዐይን ይታይ እንደነበር በኢንስቲትዩቱ የስፔስ ሳይንስ ተመራማሪ ኤፍሬም በሺር (ዶ/ር) ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በሂደት ጭጋግ መሆኑን ተከትሎ በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ብዙዎች ትእይንቱን ሲመለከቱ እንደነበርም ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ኤፍሬም ገለጻ ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ መሬት በጸሃይና ጨረቃ መካከል ስትሆን የሚከሰት ነው።
አፋር ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ለትእይንቱ ያለዉን ምቹ ሁኔታ እና ከፊል ግርዶሹን በተሻለ በጥራት ለማየት በማሰብ ከዩኒቨርስቲው ጋር በመተባበር ፕሮግራሙ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
ይህ መሆኑ አካባቢው በስፔስ ቱሪዝም ዘርፍ ያለውን አቅም ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ እስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ተወካይ አቶ ኪሩቤል መንበሩ ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዩች ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱሮህማን ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው ትዕይንቱ የዩኒቨርስቲዉን የዘርፉን ምሁራን የተሻለ አቅምና እውቀት ካላቸዉ የሀገሪቱ ተመራማሪዎች ጋር ለማቀራረብ ያስችላ ብለዋል፡፡