በኢትዮጵያ በፀሃይ ብርሃን ላይ ክብ ስርቶ የተስተዋለው “ሰን ሃሎ”
“ሰን ሃሎ” ዛሬ ረፋድ ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተስተውሏል
ለመሆኑ “ሰን ሃሎ” ምንድን ነው፤ እንዴትስ ይከሰታል?
በዛሬው እለት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የፀሃይ ብርህን ላይ ክብ የሰራ ሌላ ነጸብራቅ በመስተዋሉ ክስተቱ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሰዎችም ይህንን ከስተት በእጅ ስልካቸው ፎቶ ግራፍ በማንሳት እንደ ፌስቡክ ባሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሲያካፍሉ ውለዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በሐረር፣ ጅግጅጋ እና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ክስተቱን የተመለከቱ ሰዎች በስፋት ፎቶ ግራፍ በማንሳት በማህባራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ አጋርተዋል።
በአዲስ አበባ ክስተቱ ዛሬ ረፋድ ላይ ለአንድ ሰዓት ደገማ የተስተዋለ ሲሆን፤ በፀሃይ ዙሪያ የቀስተ ደመና ቀለም ያለው ነፀብራቅ መታዩቱንም ተመልክተናል።
“ሰን ሃሎ” ምንድን ነው?
አንዳንዶች ይህንን ምልክት “መጥፎ ነገር ሊከሰት መሆኑን ማሳያ ነው፤ ወደ ፈጣሪ እንጸልይ” ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ክስተቱን “ተዓምራዊ” አድርገው ይወሰዱታል።
የዘርፉ ተመራማሪዎች በበኩላቸው “ሰን ሃሎ” በከባቢ አየር ውስጥ ተበትነው በሚገኙ ባለ ስድስት ጎን የበረዶ ክሪስታሎች ላይ ፀሐይ ብርሃን በሚያንፀባርቅበት ወቅት የሚከሰት ነው ይላሉ።
“ሰን ሃሎ” ከቀን በተጨማሪም በምሽት ላይ በጨረቃ ዙሪያ የሚከሰት ሲሆን፤ በነጭ አሊያም በቀስ ተደመና ቀለማት በክብ፣ በቅስቶች እና በነጠብጣብ ቅርጾች ሊከሰት ይችላል።
“ሰን ሃሎ” የሜትሪዮሎጂ ስርዓት ከመልማቱ በፊትም የአየር ፀባይን ለመተንበይ ይረዳ ነበር የተባለ ሲሆን፤ ለምሰሌ “ሰን ሃሎ” ከታየ በቀጣይ 24 ሰዓትት ውስጥ ዝናብ ሊዘንብ መሆኑን እንደሚያመላክትም ይነገራል።