ደምበል ኃይቅን መለያዋ ያደረገችው ባቱ (ዝዋይ) ከተማ
የባቱ ከተማን ተመራጭ የኢቨስትመንትና የቱሪዝም ማእከል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል
የባቱ (ዝዋይ) ከተማ በ1953 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገርላታል
በ1953ዓ.ም እንደተቆረቆረች የሚነገርላት የባቱ(ዝዋይ) ከተማ አሁን ላይ ሪፎርም ውስጥ ከገቡ የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ ናት። ባቱ ከተማ ከአዲስ አበባ በ160 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝና በተፈጥሮ ከታደሉ ከተሞች ውስጥ የምትጠቀስም ናት።
የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛሀኝ ደጀኔ ለአል-ዐይን ኒውስ እንደተናገሩት፤ ከተማዋ ደምበል ኃይቅ አጠገብ መገኘቷ የቱሪዝም ማእከል እንድትሆን አስችሏታል ብሏል።
“ደምበል ኃይቅ የከተማዋ መለያ ነው”ም ነው ያሉት።
ከንቲባው የጥምቀት በዓል በኃይቅ ላይ ሲካሄድና ትእይንቱ በኃይቅ ተጀምሮ በኃይቅ ሲያልቅ ማየት የሚፈጥረው ስሜት ልዩ እንደሆነም ተናግረዋል።
የጥምቀት በዓል በዚህ ዓመት ካለፉት ዓመታት በተሻለ እና በደመቀ መልኩ እንደተከበረ የገለጹት ከንቲባው፤ በመጪው ዓመት (2015 ዓ.ም) በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ከተማዋ መጥተው የበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ የከተማ መስተዳደሩ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከንቲባው የባቱ (ዝዋይ) ከተማን የቱሪዝም መስህብነት ይበልጥ ለማጉላት የግል ባለብቶች መዋእለ ንዋያቸውን በከተማዋ እንዲያፈሱ ሲሉም ጠይቀዋል።
“ኃይቁ ዳር ለኢንቨስትምንት የሚሆን 1 ሺህ 254 ሄክታር መሬት አለ፤ ከዚሁ 20 ሄክታር የሚሆነው ለኢንቨስትመንት የተዘጋጀ ነው” ሲሉም ከንቲባው ተናግረዋል።
ባቱ የቱሪዝም ማእክል ከመሆኗ በተጨማሪ “ጠንካራ የሚባል ማህበራዊ መስተጋብር ያለው ህዝብ መኖርያ ናት” ያት ከንቲባው፤ ህዝቡ የተለያየ እምነት ተከታይ ቢሆንም በደስታም ሆነ በኃዘን ሁሉንም ነገሮች በጋራ የሚያስኬሂድ “የአንድነት ተምሳሌት” ያደርገዋል ብለዋል።
በዓለም ላይ ባልተለመደ መልኩ ክርስቲያኑ፣ ሙስሊሙም ሆነ ፕሮቴስታንቱ “ቀብር የሚያስፈጽመው በአንድ ቦታ ላይ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ይህን እሴት ይዞ ለማስቀጠል የከተማ መስተዳድሩ ይሰራልም ነው ያሉት የባቱ ከተማ ከንቲባው አቶ ገዛሀኝ።