መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩ የትግራይ ከተሞች ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ በአማራጭ መንገድ ኤሌክትሪክ አግኝተዋል
ከሰሞኑ በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ነው
መቀሌን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከተሞች መብራት ማግኘታቸው ተነግሯል
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው የነበሩት የሰሜን ኢትጵያ ከተሞች ዛሬ ከምሳ ሰዓት መልስ ጀምሮ መብራት ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለአል ዐይን አማርኛ እንዳስታወቁት ከሀሙስ ዕለት ጀምሮ መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩት መቀሌ፣ አዲግራት፣ አድዋ፣አክሱም እና ውቅሮ ዛሬ መብራት አግኝተዋል፡፡
ከአላማጣ - መሆኒ- መቀሌ ከተዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመር አገልግሎት ያገኙ የነበሩት ከተሞቹ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል “እስካሁን ባላወቀው ምክንያት” መብራት ተቋርጦባቸው ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት ሕዝቡ ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረግ አካባቢዎቹ በአማራጭ መስመር የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሞገስ ከተሞቹ የመብራት አገልግሎት ያገኙት ከተከዜ ኃይል ማመንጫ ወደ መቀሌ መብራት ያደርስ የነበረው መስመር የጥገና ስራ በመጠናቀቁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ መቀሌ፣ አዲግራት፣ አድዋ፣አክሱም እና ውቅሮ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኙ ሲሆን መቀሌ ከተማ የሚገኘው የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግን መብራት እንዳላገኘ አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡
መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ መብራት ያላገኘው፤ ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ ኃይል የሚጠቀሙትን በአንድ ጊዜ ማገናኘት ስለሚያስቸግር ነው እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፡፡
ዳይሬክተሩ የአላማጣ- መሆኒ- መቀሌ መስመር የብልሽት ምክንያት መለየት እስኪቻል ድረስ ከተከዜ መቀሌ ባለው የኤሌክትሪክ መስመር መብራት በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ እንደሚያገኙ ትናንትና ገልጸው ነበር፡፡
በዚህም መሰረት በከተሞቹ ዛሬ ከሰባት ሰዓት ከ 18 ደቂቃ ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መኖሩን አል ዐይን አማርኛ አረጋግጧል፡፡