በትግራይ ክልል ካለፈው ሀሙስ ጀምሮ የመብራት አገልግሎት ተቋርጧል
አገልግሎቱ የተቋረጠበት ምክንያት እስካሁን አለመታወቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጿል
ክልሉ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥ ከተከዜ ኃይል ማመንጫ አገልግሎት እንደሚያገኝ ተቋሙ አስታውቋል
በትግራይ ክልል ካለፈው ሀሙስ ከሰዓት ጀምሮ የመብራት አገልግሎት መቋረጡን የመቀሌና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እንደገለፁት ፣ በክልሉ ከነበረው ውጊያ በኋላ የመብራት መቆራረጥ ቢያጋጥምም የአሁኑ ግን ረዘም ላሉ ቀናት መቆየቱንና መቼ አገልግሎት እንደሚጀምር መረጃ እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከባለፈው ሀሙስ ዕለት ጀምሮ በትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ መቋረጡን አረጋግጠዋል፡፡ የመብራት አገልግሎቱ የተቋረጠበትን ምክንያት ለመለየትም የጥገና ባለሙያዎች ከአርብ ዕለት ጀምሮ በመስመሩ ላይ ፍተሻ እያደረጉ መቆየታቸውን ገልጸው “በትክክል እዚህ ቦታ ላይ ይህ ችግር ነው ያጋጠመው” የሚል ሪፖርት እስካሁን አለመቅረቡንና ችግሩ በውል አለመታወቁን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ በትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ እንደማይሰራ እንጂ ለምን እንደማይሰራ የታወቀ ነገር እንደሌለ ነ ው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
ክልሉ ከአላማጣ መሆኒ መቀሌ በተዘረጋ መስመር ኤሌክትሪክ ሲያገኝ እንደነበር የገለጹት አቶ ሞገስ ፣ ከተከዜ መስመር ያለው አማራጭም ለጊዜው አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ከአላማጣ እስከ መቀሌ ባለው የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ፍተሻ ተከናውኖ የጥገና ስራውን እንደሚከናወንም አቶ ሞገስ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሞገስ፣ ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው ከተከዜ ኃይል ማመንጫ ወደ መቀሌ የነበረው መስመር የጥገና ስራው እስካሁን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ጥገናው አልቆ በጥቂት ቀናት ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ አሁን የተፈጠረውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግር መለየት እስኪቻል ድረስ ከተከዜ መቀሌ ባለው የኤሌክትሪክ መስመር ፣ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ ክልሉ መብራት እንደሚያገኝም ነው የተናገሩት፡፡
ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ለከፋ ጉዳት የሚዳረገው ሕዝቡ በመሆኑ፣ የመብራት መቋረጡ “ሆን ተብሎ የሚፈጸም” ከሆነ በቅርብ ያለው ሕዝብ ሊያስቆም እንደሚገባ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡