“ከኃላፊነት ተነስቷል ስለመባሉ የማውቀው ነገር የለም”- ዶ/ር ሙሉ ነጋ
ዶ/ር ሙሉ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚነታቸው “ተነሱ” በሚል እየተወራ ይገኛል
ዶ/ር ሙሉ በመደበኛ ስራቸው ላይ እንደሚገኙም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋን በተመለከተ መረጃዎች በተለያዩ ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች እየተዘዋወሩ ነው፡፡
ዶ/ር ሙሉ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል በሚልም ነው እየተወራ የሚገኘው፡፡
መረጃውን በተመለከተ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር ሙሉ ግን ወሬውን እንዳልሰሙ አስታውቀዋል፡፡
አሁን በመደበኛ ስራቸው ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከኃላፊነታቸው ስለመነሳታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
“አሁን ላይ በሥራ ስብሰባ ላይ እገኛለሁ” ሲሉም ነው ዶ/ር ሙሉ ለአል ዐይን አማርኛ የገለጹት፡፡
“ዶ/ር ሙሉ ከኃላፊነት ተነስተዋል” በሚል ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የተለቀቀውን መረጃ በርካቶች እየተቀባበሉት ነው፡፡
ዶ/ር ሙሉ ነጋ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የትግራይ ክልል አስተዳደርን በተመለከተ በወጣው ደንብ መሰረት ህዳር 4 ቀን 2013 ዓ/ም መሾማቸው ይታወሳል፡፡
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከመሾማቸው አስቀድሞ ከሚያዚያ 2012 ዓ.ም ጀምሮ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል።
ሚኒስትር ዴኤታ ከመሆናቸው በፊት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና በሥራ ኃላፊነት አግልግለዋል፡፡