ህወሓት አሁን ያለንበት ወቅት ከ1983 ጋር ተመሳሳይ አለመሆኑን ሊረዳ ይገባል- አምባሳደር ፌልትማን
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ ስለነበራቸው ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል
አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ገለልተኛ መሆኗንም አምባሳዳሩ ገልፀዋል
ከትናንት በስቲያ ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ ያቀኑት በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ስለቆይታቸው ከብዙሃን መገናኛዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ህወሓት ከ30 ዓመት በፊት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ መንግስቱ ሃይለማርያምን አስተዳድር በትጥቅ ትግል ከስልጣን ያነሳበትን መንገድ አሁን ለመድገም ማሰብ የለበትም ብለዋል።
“የህወሓት አመራሮች የአሁኑን ወቅት እንደሚረዱ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ይህ 1983 ዓ.ም አይደለም ሁኔታዎቹን እንዲረዱም ለህወሃት ነግረናቸዋል” ያሉት አምባሳደር ፊልትማን፤ ወደ አዲስ አበባ መግባት ከዚህ በፊት ከነበረው ይለያል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ህወሃት በትግራይ ክልል የነበረውን ሀገር መከላከያ የሰሜን እዝን ማጥቃቱን፣ የጠናጠል ተኩስ አቁም ተደርጎ ሰራዊቱ ከትግራይ መውጣቱን እና የፌደራል መንግስት በክልሉ ላሉ ተጎጂዎች እያደረገ ያለውን የሰብዓዊ መብት ድጋፎችን አሜሪካ እውቅና እንድትሰጥ እንደሚፈልጉም አምባሳደር ፌልትማን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት መስማታቸውን አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሰኔ እና መስከረም ወራት ላይ በተደረገ ምርጫ ተመርጠዋል ያሉት አምባሳደሩ “የአሜሪካ ፍላጎት ለ27 ዓመት በስልጣን ላይ የነበረውን ህወሓት መራሽ ኢህአዴግን ወደ ስልጣን መመለስ አይደለም” ብለዋል።
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሕጋዊ እና በምርጫ የተመረጡ መሪ ለመሆናቸው እውቅና እንሰጣለን፣ ይሁንና አሜሪካ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ዙሪያ ለየተኛውም አካል ውግንና የላትም” ሲሉም ከጋዜጠኞቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
“የአሜሪካ ፍላጎት ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ወደ ችግር የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ይጨምራል የሚል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይጨምራሉ እንዲሁም ሌሎች ያልተጠበቁ የኢትዮጵያን አንድነት የሚጎዱ ችግሮች ይከሰታሉ የሚሉ ስጋቶችን ለመከላከል ነው” ብለዋል አምባሳደሩ።
በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወደ ጦርነት የገቡት አካላት ወደ ስምምነት እንዲመጡ በአዲስ አበባ እና በጎረቤት ሀገራት ካሉ አመራሮች፣ዲፖሎማቶች እና ሌሎች ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ አካላት ጋር መወያየታቸውንም ተናግረዋል።
አምባሳደሩ በተናጠል ከሁለቱም አካላት ጋር መወያታቸውን ተናግረው ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን እንደሚያሸንፉ እንደነገሯቸውም ጠቅሰዋል።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የህወሃት ሀይሎች እና የፌደራል መንግስት ወደ ስምምነት ለመምጣት ፍላጎት እንዳላቸው ነግረውኛል ያሉት አምባሳደሩ ችግሩ ቀድሞ ማን ይጀምር የሚለው ነው ሲሉም አክለዋል።
ጦርነቱ አሁንም በመቀጠሉ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው ሁለቱማ አካላት ግን ለተጎጂዎች የሰብዓዊ ድጋፎች እንዲደርሱ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።