ህወሓት ከሁለቱ ክልሎች ለቆ እንዲወጣ ግፊት ሊደረግበት እንደሚገባ አቶ ደመቀ አሳሰቡ
በውይይቱ አቶ ደመቀም ጦርነት የሚቆምበትን መንገድ በተመለከተ የኢትዮጵያን አቋም አስረድተዋል
አቶ ደመቀ ጄፍሪ ፊልትማን ጋር ተወያይተዋል
ህወሓት ከሁለቱ ክልሎች ለቆ እንዲወጣ ግፊት ሊደረግበት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡
አቶ ደመቀ ከአሜሪካ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልኡክ ጄፈሪ ፌልትማን ጋር መወያየታቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
አቶ ደመቀ ከአሁን ቀደምም ፌልትማንን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረው ነበረ፡፡
“በአዲስ አበባ እና በሰሜን ያሉ ሁሉም መሪዎች ችግራቸው ፖለቲካዊ እንደሆነና ፖለቲካዊ መፍትሄን እንደሚፈልግ በግለሰብ ደረጃ ተስማምተዋል”- ኦባሳንጆ
በውይይቱ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር የሚደረገው ጦርነት ስለሚቆምበት መንገድ የአሜሪካ ሐሳብ ምን እንደሆነ በፌልትማን መነሳቱን ያስታወቀው አገልግሎቱ አቶ ደመቀም የኢትዮጵያን አቋም አስረድተዋል ብሏል።
እንደ አገልግሎቱ መግለጫ ከሆነ በኮምቦልቻ እና በላሊበላ ለሰብአዊ ርዳታ የሚውሉ በረራዎች መፈቀዳቸውን የገለጹት አቶ ደመቀ ርዳታ የጫኑ 369 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ መፈቀዱንም ተናግረዋል።
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎችን ሁኔታ በተመለከተም ውይይት መደረጉንም ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።
ህወሓት አሁንም ቢሆን በአፋር እና በአማራ ክልሎች ጥቃት እየፈጸመና ከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ስብራት እያደረሰ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሁለቱ ክልሎች ለቅቆ እንዲወጣ ግፊት ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል ተብሏል።
ሆኖም ውይይቱ በአካል ወይም በስልክ የተደረገ መሆኑን አገልግሎቱ ግልጽ አላደረገም፡፡
አሜሪካ ጦርነቱ ቆሞ ወደ ድርድር እንዲመጣ ግፊት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ አፍሪካ ህብረት በኦሊሴገን ኦባሳንጆ በኩል የሚያደርገውን የሰላም ጥረት እንደምትደግፍ ማስታወቋም አይዘነጋም፡፡