ኢኮኖሚ
የጢስ ዓባይ ባህር ዳር የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር 8 ምሰሶዎች ወደቁ
ምሰሶዎቹ በመውደቃቸው እስከ 30 ሜጋ ዋት ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት መላክ አልተቻለም
ከሰኞ ምሽት ጀምሮ በተፈፀሙ ስርቆቶች ነው ምሰሶዎቹ የወደቁት
ከጢስ ዓባይ የውሃ ኃይል ማመንጫ ወደ ባህር ዳር የተዘረጋው ባለ 132 ኮሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር ምሰሶ ላይ ስርቆት መፈተሙን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡
ከሰኞ ምሽት ጀምሮ በተፈፀሙ ስርቆቶች ስምንት ምሰሶዎች መውደቃቸውንም ተቋሙ ይፋ አድርጓል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ ያናገራቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ፣ ከሰኞ ለሊት ጀምሮ በተፈፀመ ስርቆት የስምንት ምሰሶዎች ብረቶች እየተፈቱ እና እየተሰበሩ በከፊል መሰረቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን በአካባቢው ኃይል ባይቋረጥም ምሰሶዎቹ በመውደቃቸው ከኃይል ማመንጫው በባህር ዳር ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ይላክ የነበረ እስከ 30 ሜጋ ዋት ኃይል መላክ እንዳልተቻለም አረጋግጠዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደድርን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የመስተዳድር አካላት ችግሩን እንዲያውቁት መደረጉንም አቶ ሞገስ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የወደቁትን ምሰሶዎች በመጠገን ወደነበሩበት ለመመለስ የጥገና ስራ ተጀምሯል፡፡