የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን ነገ አቡዳቢ ይገባሉ
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን፤ “ዩኤኢን ከሰኞ ጀምሬ እጎበኛለሁ፣ ይህም ወቅቱን የጠበቀ ነው” ብለዋል
ኤርዶሃን፤ አንካራ አቡዳቢ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠናከር ትፈልጋለች ብለዋል
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን በተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች የሚያደርጉትን ጉብኝት ነገ እንደሚጀምሩ አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቀርቡ ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ ሲሆን ከነገ ጀምሮም በዩኤኢ ጉብኝት ያደርጋሉ። ረሲብ ጣኢብ ኤርዶሃን በዩኤኢ በሚኖራቸው ቆይታ ከአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና ከዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
በዚህ ጉብኝትም ፤ የአቡዳቢ እና አንካራ ሁሉንም አይነት የሁለትዮች ግንኙነቶች ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።
በቱርኩ ፕሬዝዳንት ጉብኝትም የልማት ትብብሮች ውይይት እንደሚደረግም ነው የተገለጸው። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ከሁለትዮች ጉዳዮቻቸው ባለፈም ቀጣናውና ዓለማቀፋዊ ለውጦችን አንስተው እንደሚነጋገሩም ተገልጿል። የሁለቱ ሀገሮች መሪዎች የዓለም ሰላምና መረጋጋት በሚጠናከርባቸው ነጥቦች ላይ ንግግር ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን፤ ለሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት መጠናከር አስተዋጽኦ የሚዲርጉ ስምምነቶችም እንደሚፈረሙ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን በቆይታቸው ከነገ በስቲያ የቱርክ ነጸነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የሀገራቸው ኤክስፖ ላይ እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን የዱባይ ኤክስፖ 2020 ም የጉብንታቸው አካል ነው ተብሏል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት አርብ ዕለት “ዩኤኢን ከሰኞ ጀምሬ እጎበኛለሁ፣ ይህም ወቅቱን የጠበቀ ነው” ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ወደ ዩኤኢ ከባለቤታቸው ጋር እንደሚሄዱ የገለጹ ሲሆን ባለቤታቸውም ከኮሮና ያገግማሉ ብለው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል፡፡
ክትባት በመውሰዳቸው ከኮሮና ቫይረስ ማገገማቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ አሁን ሲመረመሩ ከቫይረሱ ነጻ መባላቸውን አረጋግጠዋል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ባለፈው ወር ወደ ዩኤኢ የሚደርጉት ጉብኝት ለሁለቱ ሀገራት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እንደሚሆን መግለጻቸው ይታወሳል።
ከአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና ከዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ኅዳር ላይ ቱርክን መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ጉብኝታቸውም ስኬታማ ነበር ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ፤ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በቱርክ ያደረጉትን ጉብኝት “ታሪካዊ እርምጃ” በሚል በተደጋጋሚ ሲያነሱ ነበር ተብሏል፡፡ ኤርዶሃን ሀገራቸው ከዩኤኢ ጋር ያለት ግንኙነት እንዲጠናከር እንደምትሰራ ታህሳስ ወር ላይ መናገራቸው ይታወሳል።