በኢትዮጵያ ያሉ የታጠቁ አካላት “የሰብዓዊ ሰራተኞችን ህይወት ደህንነት” እንዲጠብቁ አሜሪካ ጥሪ አቀረበች
የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን ወደ ሕግ እንዲያቀርብ ኤምባሲው ጠይቋል
ከህዳር ወር ወዲህ በትግራይ ሰባት የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች መገደላቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል
በኢትዮጵያ ያሉት የታጠቁ አካላት “የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞችን ህይወት ደህንነት” እንዲጠብቁ አሜሪካ ጥሪ አቀረበች፡፡
በኢትዮጵያ የአማሪካ ኤምባሲ በትናንታናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞችን ደህንነት የመጠበቅ ትልቅ ሚና አለው ብሏል፡፡
ኤምባሲው አክሎም አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ መሰረት ግዴታቸውን ሊውጡ እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡
ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኖች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከህዳር 2020 ወዲህ በቅርቡ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 28/2021በትግራይ ክልል ብቻ ሰባት የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች እንዲሁም በሌላ የሀገሪቱ ክፍል አንድ የሰብዓዊ ሰራተኛ መገደላቸውን ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የቅርብ ጊዜው የግድያ ታሪክ ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈጸመ ሲሆን በዚሁ ቀን አንድ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት(USAID) ሰራተኛ በትግራይ ቆላ ተምቤን መገደሉን እና ግድያው በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ወታደሮች ስለመፈጸሙ ሪፖርት መደረጉን ነው የአሜሪካ ኤምባሲ የጠቆመው፡፡
ድርጊቱን በጥብቅ እንደሚያወግዝ የገለፀው ኤምባሲው መሰል ድረጊቶች መቆም እንዳለባቸው እንዲሁም መንግስት በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ወደ ሕግ በማቅረብ ተጠያቂ ሊያደረግ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡