ምርመራው በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሊጨምር እንደሚችልም ተገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ በትግራይ ተፈጽመዋል የተባሉትን ጥሰቶች መመርመር እንደሚጀምሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ምርመራው በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሊጨምር እንደሚችል ነው ገልጿል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም አጋማሽ ከመንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ፣ በትግራይ ክልል ተፈጽሟል የተባለውን የመብት ጥሰት በጋራ ለማጣራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡
ከሁለቱም ወገን ከእያንዳንዳቸው ስድስት የመርማሪ አባላትን ያካተተ የባለሙያዎች ቡድን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ተመረጡ የትግራይ ክልል አካባቢዎች እንደሚያመራ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) መግለፃቸውንም ነው ሚኒስቴሩ የሪፖርትር ጋዜጣ ዘገባን ዋቢ በማድረግ በትዊተር ገጹ ያሰፈረው፡፡
የመርማሪ ቡድኑ አባላት ለምርመራ የሚያስፈልጉ የቅድመ መረጃ ማሰባሰብ፣ የቦታ ልየታ፣ የምርመራ ሥልቶችን መለየትና የትራንስፖርት ሁኔታዎች ላይ ሲመክሩ መቆየታቸውንም ነው ዋና ኮሚሽነሩ አክለው የገለጹት፡፡
ከ12 የመርማሪ ቡድኑ አባላት በተጨማሪ የሕግ፣ የሥርዓተ ፆታ፣ የደኅንነትና የትርጉም ባለሙያዎችን ጨምሮ የምርመራ ቡድኑ 30 ያህል አባላት ይኖሩታልም ተብሏል፡፡
ኢሰመኮ እና ተመድ በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰበት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ያለውንየሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ኢሰመኮ ቀደም ሲልም በማይካድራና በአክሱም ከተማ አካሄድኩት ባለው ገለልተኛ ምርመራ፣ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን እንዳረጋገጠ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
በመንግሥት አነሳሽነት ላለፉት ሁለት ወራት ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተውጣጡ አባላት የተቋቋመ የምርመራ ቡድን፣ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋ ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረው ነበር፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የአክሱም ጭፍጨፋን በተመለከተ ይፋ ባደረገው የመጀመርያ ምዕራፍ የምርመራ ውጤት መሰረት በኤርትራ ወታደሮች፣ በሕወሓት ኃይሎችና በመከላከያ ሠራዊት ውጊያ ምክንያት 99 ሰዎች መገደላቸውን አል ዐይን መዘገቡም የሚታወስ ነው፡፡