የአሜሪካ ሴኔት በትግራይ ክልል ጉዳይ 10 ነጥቦችን ያካተተ የውሳኔ ሀሳብ አሳለፈ
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትቴር በኢትዮጵያ ላይ “ተገቢ ያልሆኑ” ያላቸው ጫናዎች እየተደረጉ መሆኑን ዛሬ ገልጿል
ሴኔቱ በትግራይ ክልል ያለው ግጭት በፍጥነት እንዲቆም እና ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ ጠይቋል
የአሜሪካ የላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) ለኢትዮጵያ መንግስት ፣ ለሕወሓት እና ለሌሎች የትግራይ ክልል ግጭት ተሳታፊዎች ሁሉ በሚል ባወጣው የውሳኔ ሀሳብ ሁሉም ግጭት እንዲያቆም ፣ የሰብአዊ መብቶችን እንዲጠብቁ ፣ ያልተቆጠበ የሰብዓዊ መብት ተደራሽነት እንዲኖር እንዲሁም በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በተፈጠረውን ግጭት በተፈጸሙ “ተዓማኒነት ያላቸው የጭካኔ ድርጊቶች” ላይ ለሚደረጉ ገለልተኛ ምርመራዎች እንዲተባበሩ የሚል ጥሪ አቅርቧል፡፡
‘የሴኔቱ የውሳኔ ሀሳብ 97 (Senate Resolution 97)’ በሚል ስያሜ የወጣው የውሳኔ ሀሳብ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለተከሰተው ግጭት መንስኤ ካላቸው ነጥቦች ጀምሮ ግጭቱ እስካስከተለው ጉዳት ሴኔቱ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያና አሜሪካ ከምዕተ ዓመት የዘለለ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን እና በአፍሪካ ሁለተኛዋ ብዙ ህዝብ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንደምትጫወት እንዲሁም ለተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮም ከፍተኛ የሰላም አስከባሪ ሰራዊቶችን የምታዋጣ መሆኑን በአዎንታዊነት ገልጿል፡፡
በመቀጠልም ሴኔቱ በትግራይ ያለው ግጭት ዕልባት እንዲያገኝ ያስችላሉ ያላቸውን 10 የውሳኔ ሀሳቦች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ከእነዚህም የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለው ግጭት በፍጥነት እንዲቆም የሚል ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በንጹኃን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በጽኑ አውግዟል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ሴኔቱ ፣ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እና ሙሉ በሙሉ እንዲያወጣ ጥሪ አቅርቦ ፣ በኤርትራ ወታደራዊ ኃይል ወይም በማንኛውም በትግራይ ወይም በሌላ የኢትዮጵያ ስፍራ ባሉ ሌሎች ኃይሎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ፣ ግድያዎች ፣ ዘረፋዎች ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ወንጀሎችን በጽኑ እንደሚያወግዝ ገልጿል፡፡
በአራተኛነት በኢትዮጵያ መንግስት እና በሕወሓት መካከል ያለው የፖለቲካ ውዝግብ ወደ ውጊያ ደረጃ ማደጉን በጥብቅ ተቃውሟል፡፡
አምስተኛ ላይ የተጠቀሰው ደግሞ በመላው የትግራይ ክልል እና በሌሎች ግንኙነቶች በተቋረጡባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉ የኤሌክትሪክ ፣ የባንክ ፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በፍጥነትና በተሟላ ሁኔታ እንዲመለሱ የሚል ነው፡፡
በስድስተኛነት ሱዳን ግጭቱን በመሸሽ የሄዱ ስደተኞችን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን አድንቋል፡፡
የኢትየጵያ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማሻሻል ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ እንዲያደርግ እንዲሁም ለትግራይ ክልል እና ለቀጣናዊ መረጋጋት ስጋት የሆኑ ሌሎች ጉዳዮችን በመከላከልም ለውጥ እንዲያመጣ በሰባተኛነት አሳስቧል፡፡
ስምንተኛ ላይ የተጠቀሰው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት በቁጥጥር ስር የሚውሉ የሕወሓት አባላትን በተመለከተ የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፍ ሕጎች መከበር አለባቸው ብሏል ሴኔቱ። በተጨማሪም መንግስት የኤርትራ ወታደሮች በአስቸኳይ እና ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ ጥያቄ እንዲያቀርብ እና በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ደጋፊዎቻቸውን፣ ማህበራዊ አንቂዎች እንዲፈታ ጠይቋል፡፡ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድም ነው ሴኔቱ የጠየቀው።
ዘጠነኛ ላይ የሰፈረው የሤኔቱ ሀሳብ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊዎች ግጭት እንዲያቆሙ፣ የሰብዓዊ አገልግሎት ተደራሽነትን እንዲያረጋግጡ እና ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ለሚደረጉ ነጻ እና ግልጽ ምርመራዎች ትብብር እንዲያደርጉ የሚል ነው፡፡
አስረኛ እና የመጨረሻ በሆነው ምክረ ሀሳቡ ፣ ሴኔቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ የገንዘብ ሚንስትር፣ ዩኤስኤይድ (USAID) እና ለዓለም አቀፍ ልማት የአሜሪ አስተዳደር ኤጀንሲ ከሌሎች የአሜሪካ የፌደራል መስሪያ ቤቶች አስተዳደር ጋር በመተባበር በግጭቱ የተሳተፉ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች እንዲጠቀሙ ጠይቋል፡፡ ለዚህም ከዓለም አቀፍ አጋሮች እና ድርጅቶች ጋር እንዲሰሩም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፣ በትግራይ ክልል ካለው ጉዳይ እና ከግድቡ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ “ተገቢ ያልሆኑ” ያሏቸው ጫናዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከጫናዎቹ መካከልም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ እና ሕወሓትን በሚደግፉ ቡድኖች የሚደረጉ ጫናዎች እንደሚገኙበት ነው የገለጹት፡፡
“ከሕወሓት ጋር ጭምር ተነጋገሩ የሚል” ሀሳብ በአሜሪካ በኩል መነሳቱን አምበሳሳደር ዲና ገልጸዋል።
ሕወሓት በቅርቡ ሽብርተኛ ተብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፈረጁ ይታወሳል፡፡