አምዶም ገብረ ስላሴ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊነታቸው ተነሱ
አምዶም የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ እና ሉዓላዊነት ቃል አቀባይ መሆናቸው የሚታወስ ነው
ምክትል ቢሮ ኃላፊው “የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አይደለም ከኃላፊነት ያነሳኝ” ብለዋል
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረስላሴ ከኃላፊነት መነሳታቸውን አስታወቁ፡፡
በገዛ ፈቃዳቸው አለመልቀቃቸውን በተለይ ለአል ዐይን አማርኛ የገለጹት አቶ አምዶም ፓርቲያቸው ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ እና ሉዓላዊነት ከሰሞኑ ከሰጠው መግለጫ እና እርሳቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ካደረጓቸው ቃለ መጠይቆች ጋር በተያያዘ ከኃላፊነት መነሳታቸው እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ተደፈሩ የተባሉ የትግራይ ሴቶችን በተመለከተ አደረግሁ ባሉት ንግግር እና ከሰሞኑ ወደ ክልሉ አቅንቶ ከነበረ ዓለም አቀፍ የሚዲያዎች ቡድን ጋር በተያያዘ ከተፈጠሩ ግርግሮች ጋር በተያያዘ መነሳታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
አቶ አምዶም “የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አይደለም ከኃላፊነት ያነሳኝ” ሲሉ ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው “አላውቀውም” የሚሉት “የፌዴራል ሚዲያ ኮሚቴ” ለጊዜያዊ አስተዳደሩ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት መነሳታቸውንም ነው የሚገልጹት፡፡
ይህንንም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ትናንት ማታ ቢሯቸው ጠርተው እንደነገሯቸው እና ደብዳቤ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
በእርምጃው ቅር የሚላቸው ምንም ዐይነት ነገር እንደሌለ የገለጹም ሲሆን በአረና አመራርነታቸው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የኮንስትራክሽን፣ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ በተመሳሳይ መልኩ ከኃላፊነት መነሳታቸውንም ነው አቶ አምዶም ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት፡፡