ዩኤኢ በ 2024 ወደ ጨረቃ የመጀመሪያውን የአረብ ልዑክ እንደምትልክ አስታወቀች
ለአረቡ ዓለም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የምታስተዋውቀው ዩኤኢ በዓለምም ተወዳዳሪነቷን እያሳደገች ነው
ሀገሪቱ በቀረጸችው የ10 ዓመት የጠፈር ምርምር ስትራቴጂ የሕዋ ተደራሽነቷን ለማሳደግ አቅዳለች
ዩኤኢ በ 2024 ወደ ጨረቃ የመጀመሪያውን የአረብ ልዑክ እንደምትልክ አስታወቀች
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እ.ኤ.አ. በ 2024 የመጀመሪያውን የአረብ ልዑክ (ሚሽን) ወደ ጨረቃ ለመላክ ማቀዷን ትናንት ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም አስታውቃለች፡፡
ወደ ጨረቃ የሚላከው ልዑክ በመሐመድ ቢን ራሺድ የጠፈር ማእከል የ 10 ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ዉስጥ የተካተተ ሲሆን በስትራቴጂው ተጨማሪ በኤሚሬቶች የሚገነቡ ሳተላይቶች እና የጠፈርተኞች ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታም ተካቷል፡፡
የዩኤኢ የመጀመሪያው ጠፈርተኛ ሀዛ አል ማንሱሪ በልምምድ ላይ
ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዱባይ ገዥ ሼክ መሐመድ ቢን ራሺድ ከ 2021-2031 የሚቆየው ዕቅዱ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለጹ ሲሆን እነዚህም-የሕዋ ተልዕኮዎች (ወደ ሕዋ ሰዎችን መላክ) ፣ ምርምርና ልማት እንዲሁም ዘላቂነት ናቸው፡፡
ሼክ መሐመድ ቢን ራሺድ በ10 ዓመት ዕቅድ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ
በስትራቴጂው ውስጥ የተዘረዘሩት የጠፈር ተልዕኮዎች እ.ኤ.አ. በሐምሌ ወር ከጃፓን የተወነጨፈው እና እ.ኤ.አ. የካቲት 2021 ወደ ማርስ እንደሚደርስ የሚጠበቀውን የ”ሆፕ ፕሮብ” ፣ ተጨማሪ የአካባቢ ጥበቃ ናኖሜትሪክ ሳተላይቶች ፣ የኤሚሬቶች የጨረቃ አሰሳ ፕሮጄክት እና ሁለተኛ የጠፈርተኞች ተልዕኮን ያካተቱ ናቸው፡፡
ሀዛ አል ማንሱሪ ከሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ጋር
በኤሚሬቶች የጨረቃ አሰሳ ፕሮጄክት በ 2024 ወደ ጨረቃ የመጀመሪያውን የአረብ ልዑክ በሀገሪቱ አቅም ይላካል ተብሎ ነው የታቀደው፡፡
ይሁንና ፣ ዘ ናሺናል እንደዘገበው ፣ ልዑኩ ሰው ይዞ አሊያም ሰው አልባ ሆኖ ስለመጓዙ የተባለ ነገር የለም፡፡
ተጨማሪ ዝርዝሮች በጊዜው እንደሚገለፁ ሼክ መሐመድ በትዊተር ገፃቸው ጽፈዋል፡፡