ሩሲያ የክሬምያን ካርታ ያካተተው የዩክሬን ማልያ “ፖለቲካዊ ትንኮሳ” ነው ስትል አውግዛለች
የዩክሬን ብሔራዊ ቡድን ማልያ እንዳስቆጣት ሩሲያ ገለጸች፡፡ ሩሲያን ያስቆጣት የዩክሬን ብሔራዊ ቡድን ለዩሮ-2020 ባዘጋጀው ማልያ ክሬምያን ያከተተ ካርታ ይዞ መምጣቱ ነው፡፡
የዩክሬን ማልያ ላይ ያለው ካርታ ወደ ሩሲያ የተጠቃለለችውን የክሬምያ ግዛት ከማካተቱም ባለፈ “ድል ለዩክሬን” የሚል መልዕክትም የተፃፈበት ነው፡፡
ሩሲያ እ.ኤ.አ በ2014 የክሬምያን ግዛት ከዩክሬን በመውሰድ የግዛቷ አካል አድርጋለች ፤ ምንም እንኳን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ባይሰጣትም፡፡
እናም አሁን የዩክሬን እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በማልያው ይዞት የወጣው ካርታ “ፖለቲካዊ ትንኮሳ” እንደሆነ ነው አንድ የሩሲያ ፓርላማ አባል የተናገሩት፡፡
የዩክሬን ብሔራዊ ቡድን ማልያ ከክሬምያ በሻገር ፣ ሌሎች በተገንጣይ ኃይሎች ስር የሚገኙ እንደ ዶኔስክና ሉጋንስክ የመሳሰሉ ግዛቶችንም ማካተቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን “ማልያ” በሀገሪቱ የእግር ኳስ ማህበር ኃላፊ አንድሬ ፓቬልኮ አማካኝነት በትላንትናው ዕለት በፌስቡክ ይፋ ተደርጓል፡፡
“ድል ለዩክሬን” የሚለው ፅሁፍ ከማልያው ጀርባ የተፃፈ ሲሆን ፣ መፈክሩ እ.ኤ.አ በ 2014 ፐሬዝደንት ቪክቶር ያኑኮቪችን ለማውረድ በተደረገ ተቃውሞ ላይ ሰልፈኞች ሲጠቀሙበት የነበረ ነው፡፡
የዬክሬን እግር ኳስ ማህበር ኃላፊ አንድሬ ፓቬልኮ፡ በመለያው ላይ ያለውን ካርታ እና መፈክር “ተጨዋቾቻችን ጥንካሬ እንዲኖራቸውና ለመላ ዩክሬን እንዲጫወቱ የሚያደርግ ነው የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ ማሪያ ዛካሮቫ ግን ፣ ማልያውን “ የዩክሬን ብሔራዊ ቡድን የክሬምያን ግዛት ያካተተ ካርታ ይዞ መዘጋጀቱ የማይሆን ነገርን እንደማለም ይቆጠራል” ሲሉ አጣጥለውታል ።
“ፍጹም ልክ ያለሆነ” በማለት ድርጊቱን ያወገዙት የሩሲያ ፓርላማ አባሉ ዲሜትሪ ስቪሽኮቭ በበኩላቸው የዩሮ-2020 አዘጋጆች ኣና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በዩክሬን ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ በሚገኙበት ወቅት አወዛጋቢውን ስፍራ ይዞ የታየው የዩክሬን ቡድን ማልያ ሩሲያን ክፉኛ አስቆጥል፡፡
በኮሮና ምክንያት ተራዝሞ የቆየው የአውሮፓ ዋንጫ (ዩሮ- 2020) ከጥቂት ቀናት በኋላ የፊታችን አርብ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ይጀመራል፡፡
በወጣው መርሀ-ግብር መሰረትም ውድድሩ ከሰኔ 4 እስከ ሀምሌ 4 በ 11 ከተሞች የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ሩሲያዊቷ ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ የውድድሩ ጨዋታ ከሚካሄድባቸው የአውሮፓ ከተሞች እንዷ ናት፡፡