ፑቲን የፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት “ቀጠናውን ለማተራመስ ያለመ ነው” አሉ
ፕሬዝዳንቱ፤ ምዕራባውያን በእስያ-ፓሲፊክ ቀጠና “ኔቶ”ን የሚመስል ቡድን ለመገንባት እየሞከሩ ነው ሲሉም ከሰዋል
ፑቲን፤“አውኩስ የተሰኘው የሶስትዮሽ የጸጥታ ስምምነት” የምዕራቡ ዓለም ፍላጎት አንዱ ማስፈጸሚያ ነው ብለዋል
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ “በቻይናዋ ታይዋን ግዛት” ያደረጉት ጉብኝት "የአንድ ሀላፊነት የጎደላቸው ፖለቲከኞች ጉዞ ብቻ ሳይሆን አላማ ያለው እና አሜሪካ በቀጣናውም ሆነ በዓለም አለመረጋጋትን ለመፍጠር እና ትርምስ ለመዝራት የሄደችበት የተጠና ስትራቴጂ ነው" ሲሉ ተናገሩ።
ፑቲን ይህን ያሉት ቻይና፣ ሩሲያ እና ኢራንን ጨምሮ 12 ሀገራት እየተሳተፉበት ባለውና ከነሃሴ 13 አስከ 27 ቀን በሚቆየው የ2022 ዓለም ጦር ሰራዊት የልምምድ መድረክ ላይ ነው።
- ፕሬዝዳንት ፑቲን ምእራባውያን በእስያ አዲስ "ኔቶ" አይነት ጥምር የጦር ለመፍጠር ይፈልጋሉ ሲሉ ከሰሱ
- "አጋሮቻችንን ለማስታጠቅ ዝግጁ ነን" - ፕሬዝደንት ፑቲን
የሩሲያው ፕሬዝዳንት በአውስትራሊያ፣ በብሪታንያ እና በአሜሪካ መካከል የተደረገውን የAUKUS (አውኩስ) የጸጥታ ስምምነት በምዕራቡ ዓለም በእስያ-ፓሲፊክ ቀጠና ኔቶ የሚመስል ቡድን ለመገንባት መሞከራቸውም በማስረጃነት ጠቅሰዋል።
"ምዕራባውያን ኔቶን የሚመስል ቡድን ወደ እስያ-ፓሲፊክ ቀጠና ለማስፋት እየፈለጉ እንደሆነ እናያለን፤ ለዚህ ዓላማ ማስፈጸሚያም እንደ አውኩስ እና ሌሎች የመሳሰሉ ወታደራዊ-ፖለቲካዊ ግንኙነቶች እየተፈጠሩ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
ፑቲን፤ የአሜሪካ እና አጋሮቿ ኔቶን የሚመስል ቡድን የመፍጠር ፍላጎት እንዳለቸው ሲገልጹ ይህ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ነው።
ፕሬዝዳንቱ ፤ ከቀናት በፊት በሞስኮ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት በእስያ-ፓሲፊክ ቀጠና የ"ኔቶ" አይነት ጥምር የጦር ኃይል ማደራጀት እንደሚፈልጉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
“አሜሪካ በዩክሬን ያለውን ግጭት ለማራዘም እየሞከረች ነው” ሱሉም ነበር አሜሪካን የከሰሱት፡፡
ሩሲያ ከአጋሮቿ እና ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ሀገራት ጋር በመሆን አሁን ያሉትን ዓለም አቀፍ ደኅንነት ስልቶችን ጨምሮ አዳዲስ ስልቶችን በመፍጠር ለማሻሻል እንደምትሰራ አስታውቀዋል።
“በወታደራዊው ዘርፍ ሩሲያ የጦር ሀይሏን ለማጠናከር እና የጸጥታ መዋቅሯን ለማጎልበት ቆርጣ ተነስታለች”ም ብለዋል ፑቲን።