የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ “አሜሪካ ቻይናን ለማፈን መሞከሯን ማቆም አለባት” አሉ
ብሊንክን፤ የአሜሪካ-ቻይናን ግንኙነት በኃላፊነት መምራት አለበት ብለወዋል
አሜሪካ ፤ የቻይና የሩሲያ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆን እጅጉን እንደሚያስጨንቃት ይነገራል
አሜሪካ ቻይናን ለመቆጣጠር እና ለማፈን መሞከሯን ማቆምና በሀገራቱ ግንኙነት ላይ እንቅፋት ከመፍጠር መቆጠብ አለባት ሲሉ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ተናገሩ፡፡
“ዋሽንግተን በቻይና ላይ የጫነችው የኤክስፖርት ቁጥጥሮች ህጋዊ መብቶቿን በእጅጉ እንደሚጎዳ እና መስተካከል አለበት”ም ብለዋል የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከአሜሪካው አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ጋር በዛሬው እለት በስልክ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
ብሊንከን በበኩላቸው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደህንነት እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ላይ ስላሉት ስጋቶችን ለቻይናው አቻቸው አንስተው መወያየታቸው ኤኤፍፒ ዘገቧል፡፡
አሜሪካ በሁለቱ ሀገራት መካከል ክፍት የግንኙነት መስመሮችን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ደጋግማ ስትገልጽ መቆየቷንና ቤጂንግ የሩሲያን የዩክሬን ወታደራዊ ዘመቻ ብትደግፍ አንድምታውን ምን ሊሆን እንደሚችል ያላትን ስጋት በቅርቡ መናገሯ አይዘነጋም፡፡
አሜሪካ ስጋቷን ብትገልጽም የሩሲያ ስትራቴጂካዊ አጋር እንደሆነች የሚነገርላት ቻይና በምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ መተቸቷን ቀጥላበታለች፡፡
በሩሲያ ላይ ጫና ለመፍጠር በጸጥታው ምክር ቤት በኩል በሚንጸባረቁ የውሳኔ ሃሳቦችንም ጭምር ድምጸ ተአቅቦ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ይህን የቻይና አካሄድ ስጋት የፈጠረባቸው የሚመስሉት ብሊንክንም ታዲያ የአሜሪካ-ቻይናን ግንኙነት በኃላፊነት መምራት እንዳለበት ለቻይናው አቻቸው ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን “አሜሪካ ከቻይና ጋር ግጭ አትፈልግም” ማላታቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንት ዢ ለሶስተኛ ጊዜ የቻይና መሪ ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ዋሽንግተን ከቤጂንግ ጋር ያሏት የግንኙነት መስመሮችን ክፍት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ በበኩላቸው ቻይና ለጋራ ጥቅም ከአሜሪካ ጋር ለመስራት ፍቃደኛ ናት ሲሉ መናገራቸው የቻይና መንግስት ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከቀናት በፊት በአሜሪካ - ቻይና ግንኙነት ዙሪያ ትኩረት የሚያደረገው የጋራ ብሔራዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት ከሆነ ሁለቱም ኃያላን ሀገራት ግንኙነታቸውንና ትብብር በማጠናከር ለዓለምና መረጋጋት ትልቅ ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል፡፡
ዢ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት በቅርቡ በኢንዶኔዥያ በሚካሄደው ቡድን-20 ስብሰባ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሊያደርጉት ከሚችሉት ውይይት በፊት መሆኑ ነው፡፡
የሁለቱም ኃያላን ሀገራት ከተባበሩ ለዓለም ሰላም የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ዋና ኃላፊ ከአሜሪካ-ቻይና ትብብር ውጭ የዓለም አቀፍ ቁልፍ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚደረግ 'ምንም መንገድ የለም' ብለው እንደሚያምኑ በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡