የዓለም ጤና ድርጅት ቦርድ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን በድጋሚ እጩ አድርጎ አቀረበ
ቦርዱ በኢትዮጵያ የቀረበለትን የ‘ይመርመርልኝ’ ጥያቄ በይደር ማቆየቱ ይታወሳል
ዶ/ር ቴድሮስ በራሱ በዓለም ጤና ድርጅት ቦርድ ነው በድጋሚ እጩ ሆነው የቀረቡት
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅትን እንዲመሩ በድጋሚ እጩ ሆነው ቀረቡ፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ በራሱ በዓለም ጤና ድርጅት ቦርድ ነው በድጋሚ እጩ ሆነው የቀረቡት፡፡
ይህም በመጪው ወርሃ ግንቦት 2022 ለሚካሄደው የዋና ዳይሬከተርነት ምርጫ በብቸኛነት የቀረቡ እጩ ያደርጋቸዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ምርጫውን አሸንፈው ድርጅቱን በድጋሚ በዋና ዳይሬክተርነት የመምራታቸው እድል ሰፊ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
ጀርመንን የመሳሰሉ ሃገራት ለዋና ዳይሬክተሩ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ከአሁን ቀደም ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ዶ/ር ቴድሮስ ከተጣለባቸው ሃላፊነት ውጪ በሽብርተኝነት ለተፈረጀው ህወሓት ያደላ የፖለቲካ ውግንና አሳይተዋል የሚል ክስ እና የ‘ይመርመርልኝ’ ጥያቄ ለቦርዱ አቅርባለች፡፡
ሆኖም ቦርዱ በመንግስት የቀረበውን ይህን ጥያቄ አሁን ሊመለከት እንደማይችል ትናንት አሳውቋል፡፡ ይህን ባሳወቀ በማግስቱም ነው ዶ/ር ቴሮስን በድጋሚ እጩ አድርጎ ያቀረበው፡፡
የቦርዱ ሊቀ መንበር ፓትሪክ አሞጽ በትናትናው እለት ይህንኑ የዋና ዳይሬክተሩን ምርጫ አስመልክቶ በተካሄደው ስብሰባ “ይህ እጅግ ውስብስብና ፖለቲካዊ መልክ ያለው እና ከኮሚቴው የአሰራር ሂደት ውጭ የሆነም ጉዳይ ነው” ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
ከቦርዱ 34 አባላት አንደኞቹም ይህን አባባል አልተቃወሙትም፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ለሮይተርስ ምላሽ የሰጡት የመንግስት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ድርጅቱ የቀረበለትን የምርመራ ጥያቄ ማዘግየቱን ገለልተኛ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው ሲሉ መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ዶ/ር ለገሰ አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም ቦርዱ በዋና ዳይሬክተሩ የወገንተኝነት ጉዳይ የቀረበለትን ምርመራ እንዲያደርግ በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፎች እንዳይገቡ ከልክሏል፣ ዜጎች በምግብ እና በመድሃኒት እጥረት እየሞቱ ነው ሲሉ ለብዙሃን መገናኛዎች መናገራቸው ይታወሳል፡፡