ግብጽ በራሰ በራ ሰዎች ላይ ግብር ትጥል እንደነበር ያውቃሉ?
ሀገራት የበጀት ክፍተታቸውን ለመሙላት አስገራሚና ያልተለመዱ የግብር አይነቶችን ሲጥሉ ይስተዋላል
ፈረንሳይ ለ125 አመታት የበርና መስኮት ግብር ታስከፍል እንደነበር በታሪክ ድርሳናት ተሰንዷል
መንግስታት የበጀት ክፍታታቸውን ከሚሞሉባቸው መንገዶች መካከል ግብር አንዱ ነው።
በተለያየ ወቅት ሀገራት በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ሲገቡ የሚያስተዋውቋቸው የግብር አይነቶች ግርምትን የሚያጭሩ ናቸው።
ቀጥሎ በመላው አለም ተጥለው የነበሩ አስገራሚ የግብር አይነቶች ቀርበዋል፦
ለህጻን ስም የሚከፈል ግብር
በስዊድን ለህጻን ልጅ የሚወጣ ስም አምስት አመት ሳይሞላው ወይም ሳይሞላት ግብር ተከፍሎ መጽደቅ አለበት። ለህጻኑ/ኗ የወጣው ስም ካልጸደቀ ወላጆች 770 ዶላር ቅጣት ይከፍላሉ። የስም ማስጸደቂያ ግብር የታወጀው ንጉሳዊ ስሞች ጥቅም ላይ እንዳይውሉና ህጻናት ያልተገባና እንግዳ ስም እንዳይወጣላቸው ለመከላከል ነው ተብሏል።
የበርና መስኮት ግብር
የፈረንሳይ አብዮት በፈረንጆቹ 1789 ከተጠናቀቀ በኋላ የሀገሪቱ የፋይናንስ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ሲደርስ የወቅቱ የገንዘብ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራሜል በቤቶች መስኮቶችና በሮች ቁጥር ልክ ግብር እንዲጣል ወሰኑ። የወቅቱን የበጀት ክፍተት ለመሙላት የተላለፈው ውሳኔ ለ125 አመታት ቆይቷል። የበርና መስኮት ግብር ላለመክፈል መስኮት ማስገጠም እየቀረ ሲሄድ የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት መጨመሩም ይህ አስገራሚ ግብር እንዲሰረዝ ምክንያት ሆኗል።
ብሪታንያም በ17ኛው ክፍለዘመን የመስኮት ግብር ነበራት። የግብሩ ጽንሰ ሃሳብ ከሁለት በላይ መስኮት ያለው ቤት ያላቸው ሰዎች ሃብታም ናቸው የሚል ነበር። እስከ ፈረንጆቹ 1851 የቆየው ህግ በርካታ ሰዎች በቤቶቻቸው ላይ መስኮቶችን እንዳይገጥሙ በማድረጉ ተሰርዟል።
በህይወት የመኖር ግብር
የሩዚያው ንጉስ (ዛር) ፒተር ቀዳማዊ ወይም ታላቁ ፒተር በ1718 አስደናቂ ግብር ጥለው ነበር፤ ማንኛውም በህይወት ያለው ሰው እስትንፋሱ ስለመቀጠሉ ብቻ የሚከፍለው ግብር።
መጸዳጃ ቤት የመጠቀም ግብር
ከ20 አመት በፊት የአሜሪካዋ ሜሪላንድ በመጸዳጃ ቤት ለሚኖር “የእረፍት ጊዜ” በአመቱ 30 ዶላር ግብር መጣል ጀመራለች። ይህ ግብር የተጎዱ የጽዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመጠገንና ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ ናይትሮጂንን ለመቀነስ ያለመ ነው ተብሎ ነበር።
የራሰ በራ ግብር
በግብጽ በ15ኛው ክፍለዘመን ሱልጣን ባርስቤይ ያስተዋወቁት የግብር ህግም በአለማቀፍ ደረጃ አግራሞትን ከሚጭሩ የግብር አይነቶች ተጠቃሽ ነው። ሱልጣን ባርስቤይ በካይሮ ኮፍያ ያደረጉ ሰዎችን እያስወለቁ ራሰ በራ የሆኑትን ግብር ማስከፈል ጀምረው እንደነበርና ነቀፌታው ሲበዛ እንደቆመ በታሪክ ተመዝግቧል።
የጺም ግብር
እንግሊዝ በ1535 በንጉስ ሄነሪ ስምንተኛ የጺም ግብር አስተዋውቃ ነበር። ይህን ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረጉት ግን የሩሲያው ንጉስ (ዛር) ታላቁ ፒተር ነበሩ። ጺማቸውን የሚያሳድጉ ሰዎች በአመት ከ30 እስከ 100 ሩብል ግብር እንዲከፍሉ ያደርጉ ነበር ተብሏል። ይህ ግብር ፖሊሶች ጺማቸውን ከማሳደግ እንዲቆጠቡ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑም ይነገራል።
የላም ባለቤቶች ላይ የሚጣል ግብር
ዴንማርክ ላም ያላቸው አርሶ አደሮች ላይ ግብር ትጥላለች፤ በአንድ ላይ 672 ክሮነር (96) ዶላር ታስከፍላለች። ግብሩ ላሞች ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት በካይ ጋዝ በከባቢ አየር ላይ ብክለት ያስከትላል በሚል የሚጣል ሲሆን፥ የሚሰበሰበው ገንዘብም ለአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ይውላል ተብሏል።
የጸሃይ ግብር
ጣሊያን ደግሞ ጸሃይ መሞቅ በነጻ መሆን የለበትም የምትል ትመስላለች። አንዳንድ ካፍቴሪያዎች ውጭ ላይ ጸሃይ እየሞቁ ካፑቺኖ ለመጠጣት “የጸሃይ ግብር” ጨምረው እንደሚያስከፍሉ ነው የተነገረው።