ዜለንስኪ የቡድን 7 መሪዎች በዩክሬን ያለው ጦርነት እስከ አመቱ መጨረሻ እንዲቆም ግፊት ሊያደርጉ ይገባል አሉ
የሃብታም ሀገራት ስብስብ የሆነው የቡዱን-7 ጉባኤ በጀርመን እየተካሄደ ይገኛል
ጉባኤው ከሚመክርባቸው ቁልፍ አጀንዳዎች መካከል “የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጉዳይ” አንዱ ነው
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ የቡዱን 7 መሪዎች በዩክሬን ያለው ጦርነት እስከ አመቱ መጨረሻ እንዲቆም ግፊት ሊያደርጉ ይገባል አሉ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በዛሬው እለት በጀርመን የአልፕስ ተራሮች ላይ በዝግ ስብስባ ለተቀመጡት የቡዱን-7 መሪዎች ባደረጉት የቪዲዮ ንግግር ነው፡፡
ኤ.ኤፍ.ፒ እንደዘገበው ከሆነ፤ በሩሲያ ኃይሎች ግስጋሴ ከፍተኛ ጫና ውስጥ የወደቁት ዜለንስኪ ጦርነቱ ቢያንስ በዓመቱ መጨረሻ እንዲቆም የቡድን-7 ሀገራት መሪዎች የተቻላቸውን እንዲያደርጉ ተማጽነዋል፡፡
ምእራባውያን እስካሁን በሞስኮ ላይ የወሰዱት እርምጃ በቂ ነው ብለው እንደማያምኑ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አሁንም ሀገራቱ በሩሲያ ላይ የሚጥሉትን ማዕቀብ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ሀገራቱ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን እንዲሰጡ መጠየቃቸውም ተሰምቷል፡፡
የሃብታም ሀገራቱ ጉባኤ በጀርመን እየተካሄደ ባለበት በዚህ አጋጣሚ፤ የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን መዲና የሆነችውን ኪቭን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች በሚሳዔል እየደበደቡ መሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከወታደራዊ ይዞታ አንጻር ቁልፍ የሆነቸውን የምስራቅ ዩክሬኗ ሴቬሮዶኔስክ ከተማ የተቆጣጠሩት፤ የሩሲያ ኃይሎች ወደ ለይስይቻንስክ ከተማ እየገሰገሱ መሆናቸውም ዘ-ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በዚህም በሩሲያ ኃይሎች ግስጋሴ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ጫና ውስጥ የወደቁት ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ፤ ከምዕራባውያን ሀገራት ሲጠብቁት የነበረውን የጦር መሳሪያ በመዘግየቱ “ሩሲያ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንድትሰነዝር እድል ፈጥሮላታል” ሲሉ በትናንትናው እለት መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት፤ የምእራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማእቀብ እንዲጥልና ጸረመአውሮፕላን የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን እንዲሰጥ ሲሉም ተማጽነዋል፡፡
“እውነተኛ አጋሮችችን ተመልካች ብቻ ከሚሆኑ ለምላሽ ፈጣን መሆን አለባቸው” ሲሉም ነበር የተደመጡት ፕሬዝዳንቱ።
የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ በቅርቡ የሩሲያ የሚሳዔል ጥቃቶች "በአንድ ላይ ለመቆማችን እና ዩክሬንን መደገፋችን ተገቢ እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው" ማለታቸውን ተከትሎ በቡዱን-7 እና በምዕራባውያን ሀገራት ከፍተኛ የትብብር መንፈስ እየተስተዋለ መሆኑ ይነገራል፡፡
ቀደም ሲልም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን እና የቡዱን-7 አባል ሀገራትን “ሊለያየን አስቦ ነበር፤ ነገር ግን አልተቻለውም ” ብለው ነበር፡፡
በዚህም ጉባኤው ሀገራቱ የጋራ አቋም ይዘው የሚወጡበትና የተለያዩ ቁልፍ ውሳኔዋች የሚያሳልፉበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በጉባኤው የደቡብ አፍሪካ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ህንድ እና ሴኔጋል መሪዎች በእንግድነት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡