የተመድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ በትግራይ ክልልና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ
ተመድ በኢትዮጵያ የተደረገው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም በመጠናቀቁ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል
በትግራይ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የፖለቲካ እና የሠላም ግንባታ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
የድርጅቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የፖለቲካ እና የሠላም ግንባታ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ ከፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ጋር በአዲስ አበባ ተወያተዋል።
በውይይታቸውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ የተደረገው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት መላኩንም ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ሳሕለ ወርቅ እና ሮዝመሪ ዲካርሎ በነበራቸው ቆይታም፤ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ያተኮረ ውይይትም ማድረጋቸው ተገልጿል።
እንዲሁም በትግራይ ስላለው ሁኔታ፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸውም ነው የተገለጸው።
ምክትል ዋና ጸሐፊዋ በዚሁ ወቅት፤ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በቅርብ መከታተላቸውን አንስተው በሠላም በመጠናቀቁም እንኳን ደስ ያላችሁ ማለታቸውን የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ፕሬዘዳንቷ ሣህለ ወርቅ ውይይት በተደረገባቸው ጉዳዮች ላይ ማብራርያ መስጠታቸውም ተገልጿል። በኢትዮጵያ እና በተመድ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት በየዘርፉ ማጠናከር እንደሚገባ አስምረውበታል።
ሮዝመሪ ዲካርሎ በበኩላቸው ከፕሬዝዳንት ሳሕለ ወርቅ ጋር “እጅግ ውጤታማ” ውይይት ስለማድረጋቸው በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የፖለቲካ እና የሠላም ግንባታ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ አካላት ቀጠናው እንዲረጋጋ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች መወያየታቸውን የገለጹት ሮዝመሪ ዲካርሎ ኢትዮጵያ የተመድ “ቁልፍ አጋር“ እንደሆነች አንስተዋል።
በትግራይ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ እንደሚያደርግ ያነሱት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ ከሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ጋርም ብሔራዊ አንድነት፤ ውይይትና ሰላም ግንባታ ላይ መወያየታቸውን አስታቀዋል።