“ሄቪሳይድ 2” የሚል መጠሪያ ያላት ታክሲዋን በቅርቡ በሰማይ ላይ እናያታለንም ተብሏል
የታክሲ አገለግሎትን ከመሬት ወደ ሰማይ ከፍ ያደርገዋል የተበለለት አዲሱ የበራሪ ታክሲ ቴክኖሎጂ እውን ሊሆን መቃረቡ ተሰምቷል።
የአሜሪካው ኪቲሀውክ ኩባንያ ያለ አብራሪ የምትጓዘውን በራሪ ታክሲውን ከሰሞኑ በተካሄደ የቴክኖሎጂ አውደርዕይ ለይ ይዞ ቀርቧል።
ኩብያው ይዞት የቀረበው በራሪ ታክሲ “ሄቪሳይድ 2” የሚል መጠሪያ ያላት ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የምትሰራ መሆኑ ታውቋል።
ያለ አብራሪ በሰማይ ላይ እንደምትበር የተነገረላት ታክሲዋ በአንድ ጊዜ ማሳፈር የምትችለው አንድ ሰው ብቻ እንደሆነም ሲ.ኔት የተባለ የቴክኖሎጂ መረጃዎችን የሚያቀርብ ድረ ገጽ አስታውቋል።
ካረፈችበት ቦታ ለመነሳት እና ተመልሶ ለማረፍ ምንም አይነት መንደርደሪያ ሳያስፈልጋት ቀጥታ ተነስታ ከበረረች በኋላ ወደ መሬትም ቀጥታ ተመልሳ የምታርፍ መሆኑም ተነግሯል።
ከፍጥነት አንጻርም በራሪዋ ታክሲ በሰዓት ከ90 እስከ 160 ኪሎ ሜትር መብረር የምትችል ሲሆን፤ በተለይ የትራፊክ መጨናነቅ ለሚሰተዋልባቸው አካባቢዎች እፎይታን የምትፈጥር ነው ተብሏል።
በራሪዋ ታክሲ ስራ ላይ በምትውልብት ጊዜ ልክ እንደ ሜትር ታክሲዎች በኪሎ ሜትር የምታስከፍል ሲሆን፤ ዋጋዋም ሁሉንም ያማከለ እና ተመጣጣኝ እንደሚሆን ተነግሯል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንጆቹ 2016 የተዋወቀችው በራሪዋ ታክሲ መቼ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ትውላለች የሚለው በግልጽ ባይቀመትም፤ ካሳለፍነው የፈረንጆቹ ግንቦት 2021 ጀምሮ የበረራ ሙከራ እየተደረገባት ይገኛል።