ቦኮሀራም ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ከ300 ሺህ በላይ ዜጎችን ገድሏል
በሺዎች የሚቆጠሩ የቦኮሀራም የሽብር ቡድን ታጣቂዎች እጅ እየሰጡ እንደሆነ ተገለጸ።
ቦኮሀራም የሽብር ቡድን በስፋት በናይጀሪያ ቢንቀሳቀስም በአብዛኛው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ላይ የሽብር አደጋዎችን ፈጥሟል።የናጅሪያ መንግስትም የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ለዓመታት በጥረት ላይ ቢሆንም ተማሪዎች ከሚማሩበት ትምህርት ቤት ከመታከት አላዳናቸውም።
ይሁንና አሁን ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የቦኮሀራም የሽብር ቡድን ታጣቂዎች እጅ እየሰጡ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮም ከ6 ሺህ በላይ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ለሀገሪቱ ጦር እጅ መስጠታቸው ቢቢሲ ዘግቧል።
እጅ ከሰጡ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች መካከል ኮማንደሮች እና ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች ይገኙበታል ተብሏል። እጃቸውን እየሰጡ ያሉት የሽብር ቡድኑ አባላት የሀገሪቱ ጦር መጠነ ሰፊ ዘመቻ መክፈቱን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም የሽብር ቡድኑ አዛዥ የነበረው አቡበከር ሼኩ ባሳለፍነው ግንቦት መገደሉን ተከትሎ ሊሆን እንደሚችልም ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።
የናይጀሪያ መንግስትም እጅ የሰጡ የሽብር ቡድኑ አባላትን እየተቀበለ ወደ ማገገሚያ ስፍራዎች በማስገባት ላይ መሆኑን ገልጿል።ይሁንና በርካታ ናይጀሪያዊያን እጅ በሰጡ የሽብር ቡድን አባላት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው በመናገር ላይ ናቸው።
ቦኮሀራም የሽብር ቡድን ከፈረንጆቹ 2009 አንስቶ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎችን እንደገደለ የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።