በአዲስ አበባ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያዎች እና ከፍተኛ ገንዘብ ተይዟል
በአዲስ አበባ ከተጠረጠሩ 1,127 ግለሰቦች መካከል 1,088ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል
በአንድ ወር ከ2 ሺህ 700 በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል
በአዲስ አበባ በመኖሪያ ቤቶች፣ በተቋማትና በተሽከርካሪዎች ላይ ከጥቅምት 25 እስከ ሕዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ ፍተሻና ብርበራ ከ2 ሺህ 700 በላይ የጦር መሳሪያዎችና ከ80 ሺህ በላይ ጥይቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24 ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በክልሉ የሕግ ማስከበር ስራ በተጀመረበት ከቀጣዩ ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ በአጠቃላይ 2,772 የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች ከ80ሺህ 241 ልዩ ልዩ ጥይቶች ጋር መያዛቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በእስካሁኑ ሂደት 25 የእጅ ቦንብ፣ 4 ልዩ ልዩ ፈንጂዎች ፣ 11 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 40 ሽጉጥ፣ 6 የተለያዩ ጠብመንጃዎች ከ 914 ጥይቶቻቸው ጋር ተጥለው በህብረተሰቡ ጥቆማ ከተጣሉበት ስፍራ በፀጥታ አካላት መነሳታቸውንም ገልጿል፡፡
በፍተሻ እና በብርበራ ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች ባሻገር በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ ነበር የተባለ ከ 4 ሚሊዮን 3 መቶ ሺህ በላይ ብር ፣248 ሺህ 941 የአሜሪካ ዶላር፣ 3 ሺህ 172 ዩሮ እና ከ192 ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጠቀሰው ኮሚሽኑ 178ሺህ 265 የኢትዮጵያ ብር፣ 181ሺ 900 የአሜሪካ ዶላር እና 200 ዩሮ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ከነተጠርጣሪዎች ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
ባሳለፍነው አንድ ወር ውስጥ በሕወሓት ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ጋር በተያያዘ ፣ በአዲስ አበባ ከተጠረጠሩ 1 ሺህ 127 ግለሰቦች መካከል 1ሺህ 88ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና በ1 ሺህ 938 የክስ መዝገብ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡