በአዲስ አበባ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ 800 ገደማ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ
ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት የተዘጋጁ ሰነዶች በብርበራ ወቅት መገኘታቸውም ነው የተገለጸው
ተጠርጣዎቹ ከህወሓት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብሏል
በአዲስ አበባ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ 800 ገደማ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል
ከህወሃት ቡድን ተልዕኮ በመቀበል በአዲስ አበባ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም እና ፀጥታን ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 800 ገደማ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ በተደረገ ጠንካራ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ የተያዙ ናቸው ተብሏል፡፡
በቁጥጥር ስራው 796 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል፡፡
በፍርድ ቤት የመበርበሪያ እና የመያዣ ትዕዛዝ በርካታ የጦር መሳሪዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው የኮሚሽኑ የልዩ ልዩ ህገ ወጥ ዝውውር ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ግርማ ተሰማ የተናገሩት፡፡
በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች እና የሚከሰቱ ግጭቶች በህወሃት ፊታውራሪነት እና ድጋፊ ሰጪነት የሚፈፀሙ ናቸው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
ይህንንም የሚያረጋግጡ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት የተዘጋጁ ሰነዶች በብርበራ ወቅት ተገኝተዋል፡፡
የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ጭምር ተልዕኮውን ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ እና ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወሱት ኮማንደሩ በተለያዩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤትና በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ 202 የተለያዩ የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት መያዛቸውንም ገልጸዋል፡፡
የደንብ አልባሳቶቹ በሃይማኖት አባቶች መኖሪያ ቤቶች ጭምር የተገኙ ናቸው፡፡
የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሲሉ የጥሪ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡