ኔቶ በማድሪድ ሊያካሂድ ያሰበውን ስብሰባ በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ስፔናውያን ወደ አደባባዮች ወጡ
ወታደራዊ ትብብር ላይ እንደሚያተኩር የተነገረለትን ስብሰባ በመጪው ሳምንት አጋማሽ በማድሪድ ይካሄዳል ተብሏል
ስፔናውያኑ ወቅታዊው የጂኦፖለቲካ ሁኔታ አልጣመንም በሚል ነው ወደ አደባባይ የወጡት
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪድን ጦር ወይም ኔቶ የፊታችን ረቡዕ እና ሐሙስ ስብሰባውን በማድሪድ ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።
ከዚህ ስብሰባ በፊት ስፔናዊያን በማድሪድ ጎዳናዎች ተሰባስበው የኔቶን እንቅስቃሴ የኮነኑ ሲሆን በኔቶ ያልተገባ እንቅስቃሴ ምክንያት ዓለም ወደ ከፋ ችግር እየገባች መሆኑን በሰልፉ ላይ አስታውቀዋል።
ሰልፈኞቹ እንዳሉት አለም አሁን ለገጠማት ችግር ዋነኛው ምክንያት የጦር መሳሪዎች ሽያጭ ነው፣ ኔቶም ሆነ ሌሎች አጋሮች ይሄንን ጉዳይ ተውት ሲሉ ተማጽነዋል።
የቀድሞው የስፔን ፕሬዝዳንት ኮንቻ ሀዮስ በሰልፉ ላይ እንዳሉት " በእነ አሜሪካ በሚመራው የጦር መሳሪያ ንግድ እና በሰዎች ግድያ ሰልቶኛል፣ ይህ ማብቃት አለበት። በማድሪድ የሚደረገው የኔቶ ስብሰባ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እንሰጣለን ሊል ነው። አሜሪካ ተውወን፣ እንደዛ ከሆነ ጦር መሳሪያ ሽያጭ የለም ሞትም የለም ይህን ነው እምንፈልገው" ብለዋል።
የኔቶ ስብሰባን ተከትሎ በማድሪድ ጥብቅ የደህንነት ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን ከተማዋ ወታደራዊ ሙሪዎችን ለመቀበል ሽርጉድ እያለች እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ኔቶ በማድሪድ በሚያደርገው ጉባኤ ላይ የጥምረቱ አባል ለመሆን ጥያቄ ላቀረቡት ስዊድን እና ፊንላንድ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን በቀጣይ ስለሚያደርገው ትብብር ዙሪያ በመምከር ምላሽ ይሰጣል ተብሏል።
በዛሬው የማድሪድ ሰልፍ ላይ አምስት ሺህ ሰዎች የኔቶን ስብሰባ የተቃወሙ ሲሆን ኔቶ ለሰላም ሊሰራ አይችልም ሌላ መፍትሄም የለውም ብለዋል።