የክረምቱ ኪነ ጥበብ በረከቶች
ሲኒማ እና ትያትር ቤቶች በዘንድሮው ክረምት ብዙ ስራዎችን ለተመልካቾቻቸው እያቀረቡ ነው
በኢትዮጵያ የወቅቶች ስያሜ መሰረት ክረምት የሚጀምረው በሰኔ ወር ሲሆን ሃምሌ እና ነሀሴ ደግሞ ክረምቱ የሚከብድባቸው ወራት ናቸው።
ከተለመደው ወቅት አስቀድሞ ከባድ ዝናብ ያስተናገደው የዘንድሮው ክረምት ሁለኛው ወር ላይ እንገኛለን።
በትምህርት እና በሌሎች ምክንያቶች የደከመውን አዕምሮ ዘና ለማድረግ ኪነ ጥበብ ዋነኛው መሳሪያ ሲሆን መዝናኛ ቤቶች ዝግጅቶቻቸውን አስቀድመው የጀመሩ ይመስላል።
የሲኒማ እና ትያትር ቤቶች ዝግጅት ያደሩጉባቸው ውጤቶቻቸውን ለተመልካቾቻቸው በማሳየት ላይ እንደሆኑ አልዐይን ባደረገው ቅኝት አረጋግጧል።
ብሔራዊ ትያትር፣ ዓለም ሲኒማ፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ ፣ አምባሳደር ሲኒማ እና ሲኒማ አምፔር ቅኝት ያደረግንባቸው ቦታዎች ናቸው።
ባደረግነው ቅኝት መሰረትም በአብዛኛው የፊልም መደጋገም ቢኖሩም ጥሩ ይዘት ያላቸው ፊልሞች እና ትያትሮች ለተመልካቾች እየቀረቡ ናቸው።
ብሔራዊ ትያትር ከሰኞ ውጪ በቀሪዎቹ ሁሉም ቀናት ከ8:00 ጀምሮ ስምንት ትያትሮችን ለተመልካቾች በማሳየት ላይ ይገኛል።
እሜቴ ብረቷ፣ ባቡሩ፣ ላጤው ባለትዳር፣ የአና ማስታወሻ፣ ሸምጋይ፣ ባሎች እና ሚስቶች፣ እሳት ወይ አበባ እና መንታ መንገድ የተሰኙ ትያትሮች ለተመልካቾች እየቀረቡ ያሉ ትያትሮች ናቸው።
ሌላኛው ለአዲስ አበባ የፊልም እና ትያትር ተመልካቾች እየተዝናኑበት ያለው ደግሞ በቦሌ የሚገኘው ዓለም ሲኒማ ነው።
በዚህ ሲኒማ ቤት ከ"መጋረጃው ጀርባ" የተሰኘው ትያትር እንዲሁም ጭረት፣ የአገር ሚስጢር አለኝ፣ ዘውድ ጎፈር ቁጥር 2 ፣ የሚስቶቼ ባሎች፣ ጋዜጠኛዋ እና ልባም የተሰኙ ፊልሞች በመታየት ላይ ናቸው።
ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ፊልሞችን እያሳየ ያለው የዓለም ሲኒማ በቀን በአማካኝ አራት ፊልሞችን ለተመልካች በማሳየት ላይ መሆኑን ታዝበናል።
የመንግስት ሲኒማ ቤቶች የሆኑት አምባሳደር፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ እና ሲኒማ አምፔር በተመሳሳይ ሰዓት ተመሳሳይ ፊልሞችን በማሳየት ላይ ናቸው።
በነዚህ ሶስት መንግስታዊ ሲኒማ ቤቶች ውስጥ ሲመት የተሰኘውን ፊልም ጨምሮ ጭረት፣ የአገር ሚስጢር አለኝ እና ዘውድ ጎፈር ቁጥር 2 እየታዩ ነው።
ያነጋገርናቸው ተመልካቾች እንዳሉን በሲኒማ ቤቶች ለተመልካች እየቀረቡ ያሉ ፊልሞች ተመሳሳይ መሆን እና ሲኒማ ቤቶቹ ያሉባቸው ቦታዎች ተቀራራቢ መሆኑን ተችተዋል።
ሲኒማ ቤቶች እና ትያትር ቤቶች በከተማዋ በሁሉም ስፍራዎች ቢዳረሱ ጥሩ ነበር ያሉን አስተያየት ሰጪዎቹ ከመሀል ከተማ ራቅ ያሉ ሰዎች በዝናብ እና በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ወደ ሲኒማ ቤቶች እንዳይመጡ እያደረጉ መሆናቸውንም ነግረውናል።
ከዚህ በፊት በጀሞ፣ ላፍቶ፣ መገናኛ እና ሌሎች የከተማዋ ስፍራዎች የነበሩ ሲኒማ ቤቶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተዘግተው እንደቀሩም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቅሰዋል።