ሶስቱ ሀገራት በወሳኝ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ቢግባቡም በህግ ጉዳዮች ላይ አለመስማማታቸውን ኢትዮጵያ አስታወቀች
ከተቋረጠው የዋሽንግተን የሶስትዮች ድርድር በኋላ በድጋሚ የተጀመረው ድርድር ትናንት 7ኛ ቀኑን አስቆጥሯል
ሶስቱ ሀገራት “በጣም ወሳኝ በሆኑ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መግባባት”ላይ ቢደርሱም በህግ ጉዳዮች ላይ ግን ከስምምነት አለመድረሳቸውን ኢትዮጵያ አስታውቃለች
ሶስቱ ሀገራት “በጣም ወሳኝ በሆኑ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መግባባት”ላይ ቢደርሱም በህግ ጉዳዮች ላይ ግን ከስምምነት አለመድረሳቸውን ኢትዮጵያ አስታውቃለች
የኢትዮጵያ፣የሱዳንና የግብጽ የቴክኒክና የህግ ቡድኖች ባደረጉት ወይይት “በጣም ወሳኝ በሆኑ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መግባባት”ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ውኃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ቡድኖቹ ከተወያዩ በኃላ የደረሱበትን ውጤት ለሶስትዮሹ የሚኒስትሮች ስብሰባ ሪፖርት አድርገዋል ብሏል፡፡
ሶስቱ ሀገራት በኢትዮጵያ ተቃውሞ ምክንያት ከወራት በፊት ከተቋረጠው የዋሽንግተን ድርድር በኃላ በድጋሚ ድርድር ከጀመሩ ትናንትና ሰባተኛ ቀን ማስቆጠራቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
መግለጫው ምንም እንኳን በወሳኝ ገዳዮች ላይ መግባባት ቢደረስም ስምምነቱን ሙሉበሙሉ ለማጠናቀቅ በህግ ገዳዮች ላይ መስማማት ያስፈልጋል ብሏል፡፡
የሱዳን ልኡክ ቡድን የተደረሰበትን መሻሻል ሪፖርት በማድረግ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር መመሪያ ይቀበላል ያለው መግለጫው ስብስባው የተጠናቀቀው ሱዳን ምክክሯን ከጨረሰች በኋላ ለመቀጠል በመስማማት ነው፡፡
ግድቡን በጥንቃቄ ከማስተዳደር ባሻገር ስምምነቱ ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ዘላቂ ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ መሆን እንዳለበት መግለጫው ጠቅሷል፡፡
የግድቡ ሙሌትና አስተዳደር ከአመታት በፊት ሱዳን ላይ በተፈረመው የመርሆች ስምምነት መሰረት መሆን አለበት ያለቸው ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብጽ የሶስቱንም ሀገራት የጋራ ጥቅም ባስከበረ መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጻለች፡፡
የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስቴት ያሰር አባስ (ፕ/ር) በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ በግድቡ የቴክኒክ ጉዳይ 95 በመቶ መግባባት የተደረሰበት ሲሆን መግባባት ያልተደረሰባቸው የህግ ጉዳዮች በመሪዎች ደረጃ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሰጥባቸው ለሶስቱም ሀገራት መሪዎች ተልኳል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌትና አስተዳደር የሚመለከት የመርህ ስምምነት እንጅ አስገዳጅ ስምምነት አልፈርምም የሚል አቋም ማንጸባረቋ ከሱዳንና ግብጽ ጋር ልዩነት ውስጥ መግባቷን ያሰር አባስ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡ በድርድሩ ላይ ሰፊ ልዩነት ያላት ግብጽ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት እወስደዋለሁ እያለች ነው፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ልማትን ለማፋጠን መሆኑን በተደጋጋሚ ብትገልጽም በግብጽ በኩል ከናይል የማገኘው የውኃ መጠን ይቀንሳል የሚል ቅሬታ ስታነሳ ቆይታለች፡፡ ሱዳን በአንጻሩ የግድቡን መገንባት እንደማትቃወም ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
በመጭው ሀምሌ ወር የግድቡን ውሃ ሙሌት ለመጀመር ኢትዮጵያ እቅድ አውጥታ እየሰራች ሲሆን ሱዳንና ግብጽ ስምምነት ላይ ሳይረስ ሙሌቱ መጀመር የለበትም የሚል አቋም ይዘዋል፡፡