ኢትዮጵያና ግብፅ እየተካሰሱ ባሉበት ወቅት የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣን አዲስ አበባ ገብተዋል
የሌ/ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ የኢትዮጵያ ጉብኝት ምን አንደምታ ይኖረዋል?
የግድብ ድርድር ከተጀመረ በ6ኛው ቀን ነው ሌ/ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ ለውይይት ኢትዮጵያ የተገኙት
የሌ/ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ የኢትዮጵያ ጉብኝት ምን አንደምታ ይኖረዋል?
የሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ሌተናል ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት ምክትል ፕሬዘዳንቱ አዲስ አበባ ሲገቡ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ፣ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸውና በጄነራል አደም መሐመድ አቀባበል እንደተደረገላቸው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ሌተናል ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ በቆይታቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና በወቅተዊ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ።
ሌተናል ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ በሱዳን የፖለቲካ ሽግግር ዉስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካላቸው ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉም የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው፡፡
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሱዳን አነሳሽነት የሶስትዮሽ ድርድሩ ዳግም ከቀጠለ ከ6ኛ ቀን በኋላ ነው ሌተናል ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡
እስካሁን በኢትዮጵያ ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል እየተደረገ በለው ድርድር በአንዳንድ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ቢኖርም በህጋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግን አሁንም መግባባት ላይ አልተደረሰም፡፡
ከዚህም ባለፈ ግብፅ እና ኢትዮጵያ ስምምነት ላለመደረሱ አንደኛቸው ሌላኛቸው ተጠያቂ በማድረግ እርስ በእርስ ወነጃጀላቸውን ቀጥለዋል፡፡
የግብፅ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ “ኢትዮጵያ ግትር አቋም በመያዟ የእስካሁኑ ድርድር ፍሬ አልባ ነው” ያለ ሲሆን ሀገሪቱ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሌሎች አማራጮችን ለመፈልግ መገደዷን አስታውቋል፡፡ ከነዚህም አንዱ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት መውሰድ መሆኑን ነው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ደግሞ ትናንት በሰጡት መግለጫ ግብፅ የመደራደር ልባዊ ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ ይሄን ሲያስረዱ “ግብፅ አንድ እግሯን ኒውዮርክ (የተመድ የጸጥታው ም/ቤት) ፣ አንድ እግሯን ደግሞ ድርድሩ ላይ አድርጋ መቀጠሏ በድርድሩ ስምምነት ላይ የመድረስ ፍላጎት የሌላት መሆኑን የሚያሳይ ነው” ብለዋል፡፡ የግብፅ ተደራዳሪዎች ራሳቸው በሚፈልጉት መልኩ ብቻ ስምምነት እንዲደረስ ግትር አቋም እንደያዙም አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡
ድርድሩ እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማደናገር እና በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሰደር የሚደረግ ማንኛውም ዘመቻ ወይም ኢትዮጵያ ያልተካተተችበትን በቅኝ ግዛት ላይ የተመሰረቱ ስምምነቶችን እንድትቀበል በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም ሲል የኢፌዴሪ የውሃ ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሔም ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል እምነት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ ግብፅና ሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቴን እጠቀማለሁ የሚል ጽኑ አቋም ይዛ ግድቡን መገንባቷን ቀጥላለች፡፡
ምንም እንኳን ግብፅ ስምምነት ሳይደረስ የዉሃ ሙሌት መጀመር የለበትም የሚል አቋም ብትይዝም ፣ ከሳምንታት በኋላ ግድቡን ዉሃ ለመሙላት በኢትዮጵያ በኩል ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚያርፍበት ቦታ የደን ምንጣሮ ለማካሔድ በነገው እለት ከ45 ኢንተርፕራይዞች ጋር የቦታ ርክክብ እንደሚፈጸም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገልጿል፡፡
የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም ፣ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያውን ሃይል ማመንጨት የሚያስችለው ውሃ የሚተኛበትን ቦታ ለማመቻቸት የደን ምንጣሮ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን እና በሚቀጥለው ሳምንት የደን ምንጣሮው እንደሚጀመር ለኢዜአ ተናግረዋል። የምንጣሮ ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ሌሎች 25 ኢንተርፕራይዞች በተጠባባቂነት መመዝገባቸውንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ከግድቡ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ያለው ፖለቲካዊ ዉጥረት እየተካረረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ድርድሩ እንዲቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸው ዉይይት መስማማታቸውን ተከትሎ ነው ድርድሩ በድጋሚ መካሔድ የጀመረው፡፡
ይሁንና በግብፅ እና በኢትዮጵያ አለመግባባት ምክንያት ድርድሩ ፈተና ላይ እየወደቀ መሆኑ የሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት ም/ል ፕሬዘዳንት ሌተናል ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ የመምጣታቸው አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
ሌተናል ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ሊወያዩ ከሚችሉባቸው ሌሎች ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ከሳምንታት በፊት የተፈጠረውን ግጭት የተመለከተ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው፡፡
በወቅቱ የተፈጠረው ግጭት ከዚህ ቀደምም የነበረ እና ሁለቱን ሀገራት ለጦርነት የማይጋብዝ በውይይት የሚፈታ ጉዳይ መሆኑን የሁለቱም ሀገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች መግለጻቸው ይታወቃል፡፡