በወታደራዊ ጁንታ የሚመሩ ሶስት ሀገራት ጥምረት ፈጠሩ
ሶስቱ ጎረቤት ሀገራት ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ባደረጉ ወታደሮች እየተመሩ ይገኛሉ
የኒጀር፣ የቡርኪናፋሶ እና የማሊ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጥምረት በመፍጠር እጣፈንታቸውን ለመወሰን ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል
መፈንቅለ መንግስት ባደረጉ ወታደሮች(ጁንታ) የሚመሩ ሶስት የሳህል ቀጣና ሀገራት ጥምረት ፈጥረዋል።
የኒጀር፣ የቡርኪናፋሶ እና የማሊ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በትናንትናው እለት ጥምረት በመፍጠር እጣፈንታቸውን ለመወሰን ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሶስቱ በወታደራዊ መንግስት(በጁንታ) የሚመሩ ሀገራት ጥምረት በመፍጠር ከሰፊው የምዕራብ አፍሪካ ፖለቲካዊ ጥምረት ራሳቸውን አርቀዋል።
ኢኮዋስ ቡርኪናፋሶን በመፈንቅለ መንግስት ምክንያት ከአባልነት አገደ
ሶስቱ ጎረቤት ሀገራት ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ባደረጉ ወታደሮች እየተመሩ ይገኛሉ።
ይህ የሀገራቱ አካሄድ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲመለሱ ከሚወተውታቸው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጥምረት(ኢኮዋስ) ጋር አቃቅሯቸዋል።
የቡርኪናፋሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆአችም ኬይለም ዲ ታምቤላ በኒጀር ዋና ከተማ ላይ በሰጡት የጋራ መግለጫ "ከአሁን በኋላ ከማሊ፣ ከኒጀር ወይም ከቡርኪናፋሶ ብትሆን አንድ አይነት እጣ ፋንታ አለን። አብረን እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ታምቤላ "እጣፈንታችንን መቆጣጠር የኛ ድርሻ ነው" ብለዋል።
ከአንድ ቀን በፊት የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በኒጀር የፈረንሳይ ወታደሮችን ጠቅልሎ መውጣት በሚያክብር ህዝብ ፊት ታይተዋል።
ወታደራዊ መሪዎቹ ከቀድሞ ቅኝ ገዢ ከነበረችው ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል። ይህ እርምጃ ፈረንሳይ በቀጣናውየ ያላትን ተጽእኖ የሚያሳጣ እና በሳህል ቀጣና ለአስርት አመታት የቆየውን የእስላማዊ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ የመግታት አለምአቀፋዊ ጥረት ያወሳስበዋል ተብሏል።
ከፈረንሳይ እና ከኢኮዋስ ነጻ መሆን የፈለጉት ሶስት ሀገራት 'አሊያንስ ኦፍ ሳህል ስቴትስ' የተሰኘ ጥምረት ፈጥረዋል።
የማሊ ጠቅላይ ሚኒሰትር ቾጉል ማይጋ " ዛሬ በሶስቱ ሀገራት ጦር መካከል ያለው ጥምረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል" ብለዋል።
ባለፈው ነሐሴ ወር ከአሜሪካው የቀውስ ጥናት ቡድን ኤሲኤልኢድ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በማሊ እና በቡርኪናፋስ ወታደሮች ስልጣን ከያዙ ወዲህ የአለመረጋጋት ሁኔታው ጨምሯል።