ኤምሬትስ እና ባህሬን የሶማሊያን ጦር በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል
በሶማሊያ ሞቃዲሾ በተፈጸመ ጥቃት ሶስት የአረብ ኤምሬትስ እና አንድ የባህሬን ወታደሮች ተገደሉ።
የኤምሬትስ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በመዲናዋ ሞቃዲሾ በሚገኝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ በተፈጸምው “የሽብር ጥቃት” ሁለት ወታደሮችም ቆስለዋል።
ጥቃቱን ያወገዘው ሚኒስቴሩ ከሶማሊያ መንግስት ጋር በመሆን መንስኤውን እንደሚመረምር መግለጹንም የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም ዘግቧል።
የኤምሬትስ ወታደሮች የሶማሊያ መንግስት ጦርን በማሰልጠን ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ ጥቃቱም ይህንኑ ወታደራዊ ትብብር የሚገታው አይሆንም ብሏል የኤምሬትስ መከላከያ ሚኒስቴር።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ወታደሮቿ ለተገደሉባት ኤምሬትስ የሀዘን መግለጫ መላካቸው ተሰምቷል።
ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው የሽብር ቡድን አልሸባብ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አራት ወታደሮች ለተገደሉበት ጥቃት ሃላፊነቱ እንደሚወስድ መግለጹን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በጀነራል ጎርደን የጦር ሰፈር በሚገኙት የኤምሬትስ እና ባህሬን ወታደሮች ላይ ጥቃቱን ያደረሰውም ሀገራቱ የሸሪአ ህግን በመተላለፍ የሶማሊያ መንግስትን በመደገፋቸው መሆኑን ነው ያስታወቀው።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ዳግም ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአልሸባብ ላይ ጦርነት ማወጃቸውና በርካታ ከተሞችን ከቡድኑ ማስለቀቃቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ቡድኑ ይህን እንቅስቃሴ በሚደግፉ ሀገራት ላይም በተለያየ ጊዜ ጥቃት ማድረሱ አይዘነጋም።
የሶማሊያ መንግስት በአልሸባብ ላይ የሚወስደውን እርምጃ የምትደግፈው ኤምሬትስ የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች የኤደን ባህረሰላጤ እና የአረቢያን ባህር ደህንነት ስጋት ውስጥ እንዳይጥሉት ስጋት አላት።
አልሸባብ በ2019 የዱባይ ፒ ኤንድ ኦ ፖርትስ ሰራተኛን መግደሉን ማሳወቁም ኤምሬትስን እንደ “ጠላት” መፈረጁን ያሳያል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።