የአዲዳስ ምርት የሆነው ልዩ የውድድር ጫማ 500 የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ተቆርጦለታል
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ባለፈው እሁድ በበርሊን ማራቶን ማሸነፏ ይታወሳል።
አትሌት ትዕግስት ውድድሩን በ2 ስአት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመግባት በ2019 በቺካጎ የተያዘውን የሴቶች የማራቶን ክብረወሰን ከ2 ደቂቃ በላይ ማሻሻሏም አይዘነጋም።
አትሌቷ በዚህ ውድድር የለበሰችው የአዲዳስ “ልዩ ጫማ” ለስኬቷ እንዳገዛት ከውድድሩ በኋላ ስትናገር ተደምጣለች።
“አዲዜሮ አዲዮስ ፕሮ ኢቮ 1” የሚል ስያሜ የተሰጠው የአዲዳስ አዲስ ጫማ 138 ግራም የሚመዝን ነው።
አዲሱ “ልዩ የውድድር ጫማ” ከዚህ ቀደም አዲዳስ ከሚያመርታቸው የውድድር ጫማዎች (340 ግራም የሚመዝኑ) ክብደቱ በግማሽ የቀነሰ መሆኑንም ኩባንያው ገልጿል።
የጫማው ክብደት መቀነስ ሯጮች ፍጥነታችቸውን እንዲጨምሩ ያግዛቸዋል ብለዋል የአዲዳስ የሽያጭ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ፓትሪክ ናቫ።
በበርሊን የአለም የሴቶች ማራቶን ክብረወሰን የሰበረችው አትሌት ትዕግስት አሰፋም፥ “ይሄ ጫማ (አዲዜሮ) እስካሁን ካደረግኳቸው የውድድር ጫማዎች ሁሉ እጅግ በጣም ቀላሉ ነው፤ ጫማ ያደረግኩ ሁላ አልመሰለኝም” ብላለች።
የውድድር ጫማው ምቹነት ትኩረቷን ውድድሩ ላይ ብቻ እንድታደርግ ስለማድረጉም መግለጿን ዴይሊ ሜል አስነብቧል።
አዲዳስ ለአትሌቶች ቀላል እና ምቹ አድርጌ አዘጋጅቸዋለሁ ያለውን “ልዩ የውድድር ጫማ” በ500 የአሜሪካ ዶላር በገበያ ላይ አውሎታል።
ከዋጋው ውድነት ባሻገር ኩባንያው ጫማውን ሲሸጥ “ይህን ጫማ ከአንድ ጊዜ በላይ መጠቀም አይመከርም” የሚል ማሳሰቢያን ማስከተሉ ከፍጻሜ ውድድር ውጭ የመደረጉን ጉዳይ አጠራጣሪ ያደርገዋል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ለውድድር የሚዘጋጁ ጫማዎች ከመደበኛ ጫማዎች በ3 በመቶ የሯጮችን ፍጥነት እንዲጨምር ያግዛሉ።
ተመሳሳይ የውድድር ጫማዎች እንደየአትሌቱ የተለያየ ውጤታማነት እንዳላቸውም ጥናቶች አሳይተዋል።
እንደ ናይኪ እና አዲዳስ ያሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎችም በየጊዜው ዘመናዊ እና ቀላል ጫማዎችን በማምረት ላይ ይገኛሉ።
ይህን ፉክክርም “የቴክኖሎጂ ዶፒንግ” ነው በሚል የሚከራከሩ አትሌቶች አሉ።