የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር 72 በመቶ በሚሆነው የክልሉ ግዛት መዋቅር መዘርጋቱን ገለጸ
አስተዳደሩ መዋቅር መዘርጋት ያልቻለው በአማራ ሃይሎች በተያዘው ቦታ መሆኑን ዶ/ር ሙሉ ተናግረዋል
የአሜሪካና የዩኤኤን ጨምሮ ከ50 በላይ አምባሳደሮች ስለትግራይ ሁኔታ ገለጻ ተደረገላቸው
በኢትዮጵያ የአሜሪካና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አምባሳደሮችን ጨምሮ 50 አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ተገኝተው ስለትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጻ አድርጎላቸዋል፡፡
ገለጻውን ያደረጉት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ናቸው፡፡ በክልሉ የተካሄደውን ውጊያ፣መዘዙና በቀጣይ መካሄድ ስላለባቸው ጉዳዮች ለአምባሳደሮቹ ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር ሙሉ የግጭቱ መነሻ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዙሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቁን የገለጹት ዶ/ር ሙሉ በክልሉ የተፈጸመው የዘረፋ ተግባር “ህወሓት ከእስርቤት ፈቶ በለቃቸው ከ10ሺ በላይ ሰዎች”ነው ብለዋል፡፡ በትግራይ ክልል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በመሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት መድረሱን መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡
በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን፣የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መጠገን፣ የክልሉን መንግስታዊ መዋቅር እንደገና መዘርጋትና ምርጫ ለማካሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቀጣይ ተግባራት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ዶ/ር ሙሉ እስካሁን 72 በመቶ በሚሆነው የክልል ግዛት መዋቅር መዘርጋቱና እስካሁን ያልተዘረጋበት ቦታ በአማራ ክልል ኃይሎች የተያዘው መሆኑንና ይህም መፍትሄ ያገኛል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡ አማራ ክልል በበኩሉ የአማራ ኃይል ያለበት ቦታን ከዚህ በኋላ እያስተዳደረው እንደሚቀጥልና አሳልፎ እንደማይሰጥ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት የትግራይን ክልል የሚያስተዳድረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን አሳውቆ ባካሄደው የ“ህግ ማስከበር ዘመቻ” ህዳር 19 የክልሉን ዋና ከተማ መቆጣጠሩንና ዘመቻው ማብቃቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ እስካሁን የጸጥታው ሁኔታ አለመረጋጋቱንና የአብአዊ እርዳታ ለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን የእርዳታ ድርጅቶች ገልጸዋል፡፡
መንግስት በበኩሉ በትግራይ የሰብአዊ እረዳታ እያቀረበ መሆኑንና የቀሩ የህወሓት አመራሮችን በማደን ላይ መሆኑን እየገለጸ ይገኛል፡፡ መንግስት ለአለምአቀፍ እርዳታ ድርጅቶችና ሚዲያዎች በትግራይ ያለውን ሁኔታ እንዲያዩ ክፍት ማድረጉን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡