የኦሮሚያ፣የቤንሻንጉልና የጋምቤላ ክልሎች ለትግራይ ክልል የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
የኦሮሚያ፣የቤንሻንጉልና የጋምቤላ ክልሎች የትግራይ ክልልን ለሚያስተዳድረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዘዳንት አሻድሊ ሀሰንና የጋምቤላ ክልል ፕሬዘዳንት ኡመድ ኦጂሉ በዛሬው እለት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ በመገኘት ድጋፉን አበርክተዋል፡፡
ድጋፉን የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ተቀብለዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉ ክልሎቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ የ257 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበርክቷል፡፡ የክልሉ ፕሬዘዳንት ሽመልስ አብዲሳ ርዳታው ባስረከቡበት ወቅት”በቀጣይ የከፋ ችግር ከመጣ በኦሮሚያ ክልል ልማት እናቆማለን እንጂ፤በትግራይ ህይወት አይቆምም” ብለዋል፡፡
የቤንሻንቡል ጉሙዝ ክልል የ15 ሚሊዮን ብርና ሁለት አምቡላንስ ድጋፍ ሲያደርግ የጋምቤላ ክልል ደግሞ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይና የሁለት አምቡላንስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ክልሎቹ ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
የፌደራል መንግስት የትግራይን ክልል ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን አሳውቆ ባካሄደው የ“ህግ ማስከበር ዘመቻ” ህዳር 19 የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን መቆጣጠሩንና ዘመቻው ማብቃቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ በክልሉ እስካሁን የጸጥታው ሁኔታ አለመረጋጋቱንና የአብአዊ እርዳታ ለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን የእርዳታ ድርጅቶች ገልጸዋል፡፡
መንግስት በበኩሉ በትግራይ የሰብአዊ እረዳታ እያቀረበ መሆኑንና የቀሩ የህወሓት አመራሮችን በማደን ላይ መሆኑን እየገለጸ ይገኛል፡፡ መንግስት ከሰብአዊ የርዳት ድርጅቶች በተጨማሪ ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በትግራይ ክልል ገብተው እንዲዘግቡ ክፍት ማድረጉን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡