የትግራይ ክልል አባቶች ለ6 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሰጡ
የትግራይ አባቶች የቤተክርስቲያኗን ማሳሰቢያ በመተው ኤጲስ ቆጾሳትን የሾሙት
ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትግራይ አባቶች እንቅስቃሴ እንዲያስቆም መንግስትንም ጠይቃ ነበር
በትግራይ ክልል የሚገኙ አባቶች ለ6 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትግራይ አባቶች ኤጲስ ቆጾሳትን የመሾም እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ አሳስባ ነበር።ቤተክርስቲያኗ ይህን የትግራይ አባቶች እንቅስቃሴ እንዲያስቆም መንግስትንም ጠይቃ ነበር።
የትግራይ አባቶች የቤተክርስቲያኗን ማሳሰበያ ወደጎን በመተው በዛሬው እለት በአክሱም የ6 ኤጲስ ቆጾሳት በዓለ ሲመት ማከናወናቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በዚህም መሰረት
1. ብፁእ አቡነ ሊባኖስ- የደቡብ ትግራይ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
2. ብፁእ አቡነ ናትናኤል- የምዕራብ ትግራይ ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
3. ብፁእ አቡነ ኣረጋዊ- የትግራይ መንበረ ሰላማ ቤተክህነት ዋና ፀሓፊ
4. ብፁእ አቡነ ዮሃንስ- በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካዔል ካቴድራል ቅዱስ ፍሬ ምናጦስ ኣቡነ ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅ ኃላፊ
5. ብፁእ አቡነ እምባቆም የደቡብ ምብራቅ ትግራይ ሀረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
6. ብፁእ አቡነ አትናቴዎዮስ - በአሜሪካ ቨርጂኒያ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርገው ተሾመዋል።
በትግራይ አባቶች እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፣ የትግራይ አባቶች ቤተክርስቲያኗ ጦርነት አላወገዘችም በሚል ነበር።
ቅሬታ ያነሱት አባቶችም "የትግራይ መንበረ ሰላማ ቤተክህነት" ማቋቋማቸው እና ከቤተክርስቲያኗ አደረጃጀት መውጣታቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ቤተክርስቲያኗ ከትግራይ አባቶች ጋር ያለውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረጓ ይታወሳል።
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰኔ 28፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ህዝበ ትግራይን ይቅርታ ጠይቃ ችግሩን በውይይት ለመፍታት የሉኡክ ቡድን ወደ መቀሌ መላኳ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ የቤተክርስቲያኗ ልኡክ በመቀሌ ከትግራይ አባቶች ጋር ሊያደርግ የነበረው ውይይት አለመሳካቱን እና ይህም እንዳሳዘናት ገልጻ ነበር።