ቲክ ቶክ የቢን ላድንን ደብዳቤ የሚያስተዋውቁ ቪዲዮዎችን እንደሚሰርዝ ገለጸ
ቢን ላድን በአሜሪካ ልዩ ዘመቻ በፈረንጆቹ 2011 በፖኪስታን መገደሉ ይታወሳል
ቲክ ቶክ በአሜሪካ ላይ የደረሰውን ጥቃት ምክንያታዊነት የሚዘርዝረውን የ2002ቱን የኦሳማ ቢን ላደን ደብዳቤን የሚያስተዋዉቁ ቪዲዮዎችን ነው የመሰረዝ የወሰነው
ቲክ ቶክ የቢን ላድንን ደብዳቤ የሚያስተዋውቁ ቪዲዮዎችን እንደሚሰርዝ ገልጿል።
የቻይናው የአጫጭር ቪዲዮዎች መተግበሪያ የሆነው ቲክ ቶክ የቢን ላደን ደብዳቤን ወይም 'ሌተር ቱ አሜሪካ' የሚስተዋውቁ ቪዲዮዎችን እንደሚሰርዝ አስታውቋል።
ቲክ ቶክ በአሜሪካ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተገቢነት የሚዘረዝረውን የ2002ቱን የኦሳማ ቢን ላደን ደብዳቤን የሚያስተዋዉቁ ቪዲዮዎችን የሚሰርዝ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ 20 አመታት ያስቆጠረው ደብዳቤ ሰሞኑን መነጋገሪያ የሆነው በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ምክንያት ነው። በምዕራቡ አለም የሚኖሩ የተወሰኑ ተጠቃሚዎች ይዘቱን ሲያደንቁት ተስተውለዋል ተብሏል።
አል ቃኢዳ ለ3000ሰዎች ምክንያት የሆነውን 9/11 ጥቃት ካደረሰ በኋላ ተጽፏል የተባለው ይህ ደብዳቤ አሜሪካን ለእስራኤል በምታደርገው ድጋፍ ተችቷል፣ የፍልስጤማውያንን "ጭቆና" በገንዘብ እየረጃች ነው የሚል ክስም አቅርቧል።
በተጨማሪም ደብዳቤ ጸረ-ሴማዊነት የሚያንጸባርቅ ይዘትም እንደተካተተበት ተጠቅሷል።
ቢን ላድን በአሜሪካ ልዩ ዘመቻ በፈረንጆቹ 2011 በፖኪስታን መገደሉ ይታወሳል።
"ይህን ደብዳቤ ማስተዋወቅ የትኛውንም የሽብር ድርጊት አንደግፍም የሚለውን ህጋችንን ይጥሳል" ያለው ቲክ ቶክ በከፍተኛ መጠን መሰራጨቱ ትክክል አለመሆኑን ገልጿል።
በትናንትናው እለት 'ሌተር ቱ አሜሪካ' የሚለው ርዕስ በቲክ ቶክ ሲፈለግ ውጤት አያስገኝም፤ "ይዘቱ መመሪያችን ሊጥስ ይችላል" የሚል ማስታወቂያም አብሮ ተለቋል።
የተወሰኑ የአሜሪካ ሴናተሮች ቲክ ቶክ እርምጃ እንደሚወስድ ከመግለጹ በፊት ቴክ ቶክ ይታገድ በማለት ከዚህ ቀደም ሲያቀርቡት የነበረውን ትችት ደግመውታል።
የዲሞክሳቲክ ተወካይ የሆኑት ጆሽ ጎታመር በኤክስ ወይም ቀድሞ ቲዊተር በሚባለው ማህበራዊ ሚዲያቸው ቴክ ቶክ በአሜሪካ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የአሸባሪዎችን ፕሮፖጋንዳ እየተጠቀመ ነው የሚል ክስ አቅርቧል።
የኃይት ሀውስ ቃል አቀባይ አንድሬው ባትስ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ሰይጣናዊ እና ጸረ-ሴማዊ ውሸቶችን ለማሰራጨት ምክንያት ማቅረብ አይቻልም ብለዋል።
የእንግሊዙ ጋዜጣ ዘጋርዲያንም በ2002 አትሞት የነበረውን የቢን ላደን ደብዳቤ ማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨበት መንገድ መሉ ስእል አይሰጥም በሚል ርብዕ እለት ሰርዞታል።