ቲክቶክ ተጠቃሚዎች የ60 ደቂቃ ቪዲዮ እንዲጭኑ ለመፍቀድ ሙከራ እያደረገ መሆኑን ገለጸ
ቲክቶክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2017 በአሜሪካ ሲጀምር 15 ሰከንድ ብቻ የሚቆይ ቪዲዮ ነበር መጫን የሚቻለው
የቲክቶክ ኩባንያ አዳዲሰ አሰራሮችን ቋሚ ከማድረጉ በፊት ሁልጊዜም ሙከራ እንደሚያካሂድ ገልጿል
ቲክቶክ ተጠቃሚዎች የ60 ደቂቃ ቪዲዮ እንዲጭኑ ለመፍቀድ ሙከራ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።
በአጫጭር ቪዲዮዎች ተወዳጅነትን ያተረፈው ቲክቶክ፣ ተጠቃሚዎች እስከ 60 ደቂቃ የሚረዝም ቪዲዮ እንዲጭኑ ለመፍቀድ ሙከራ እያደረገ መሆኑን ያሆ ቴክ ዘግቧል።
ቲክቶክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2017 በአሜሪካ ሲጀምር 15 ሰከንድ ብቻ የሚቆይ ቪዲዮ ነበር መጫን የሚቻለው። ነገርግን ንብረትነቱ የቻይናው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባይቲዳንስ የሆነው ቲክቶክ ከእዚያ ጀምሮ ባሉት አመታት ገደቡን እያሻሻለ አሁን ላይ ተጠቃሚዎች ለ10 ደቂቃ የሚቆይ ቪዲዮ እንዲጭኑ ፈቅዷል።
ባለፈው ጥር ወር ደግሞ የተወሰኑ የኮንቴንት ክሬተሮች ወይም ይዘት አዘጋጆች 30 ደቂቃ የሚረዝሙ ቪዲዮዎች እንዲጭኑ የፈቀደ ሲሆን ሰብስክሪፕሽን(አባልነት) የሚሸጡ ደግሞ እስከ 20 ደቂቃ የሚረዝም ቪዲዮዎችን እንዲጭኑ መፍቀዱ ይታወሳል።
ቲክቶክ አሁን ላይ የሚጫኑ ቪዲዮዎችን የጊዜ እርዝማኔ በድጋማ ስለመጨመር እያሰበ ነው።
ቲክቶክ ባለፈው አርብ እለት ለሲቢኤስ ኒውስ እንዳረጋገጠው ይህ ማሻሻያ በቅርቡ ይለቀቃል ተብሎ ባይገመትም፣ የተወሰኑ ተጠቃሚዎች አሁን የ60 ደቂቃ ቪዲዮ መጫን ይችላሉ።
አሁን የሙከራ ወቅት ላይ መሆኑን የገለጸው የቲክቶክ ኩባንያ አዳዲሰ አሰራሮችን ቋሚ ከማድረጉ በፊት ሁልጊዜም ሙከራ እንደሚያካሂድ ገልጿል።
የማህበራዊ ሚዲያ አማካሪ የሆነው ማት ናቫራ ቲክቶክ ሙከራ መጀመሩን የሚያሳይ መልእክት ከደረሳቸው ውስጥ አንዱ ነው። "እስከ 60 ደቂቃ የሚረዝም ቪዲዮ ጫን። መተግበሪያው አፕቱዴት ወይም የተሻሻለ መሆኑን ካረጋገጥህ በኋላ ከመተግበሪህ ወይም ከዴስክቶፕ ቲክቶክ.ኮም(tiktok.com) ጫን" ይላል ለናቫራ የደረሰው መልእክት።
የቲክቶክ በአጫጭር ቪዲዮዎች ተወዳጅነት ማግኘት እንዲሜታ እና ዩቲዩብ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ተመሳሳይ የሆነ የአጭር ቪዲዮ ማጋሪያ ፕላትፎርሞችን እንዲጨምሩ አስገድዷቸዋል። ቲክቶክ በአንጻሩ በአሜሪካ ያለው እጣፈንታ እክል የገጠመው ቢሆንም ቀስእያለ ረዘም ያሉ ይዘቶች እንዲጫኑ እያደረገ ነው።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባይትዳንስ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የማይሸጠው ከሆነ ቲክቶክ በአሜሪካ እንዲታገድ የሚያስችል ህግ ፈርመዋል።
ቲክቶክ እና ባይቲዳንስ በሰጡት ምላሽ እርምጃው ህገመንግስታዊ አይደለም በማለት ክስ አቅርበዋል።