አሜሪካ የመንግስት ተቋማት በ30 ቀናት ውስጥ የቲክቶክ መተግበሪያን እንዲያስወግዱ የሚያስገድድ መመሪያ አወጣች
መመሪያው የአሜሪካን ህዝብ ደህንነት እና የግል ሚስጥርን ለመጠበቅ የሚያስችል ነው ተብሏል
ካናዳ፣ አውሮፓ ህብረት እና ታይዋን በቲክቶክ ላይ ተመሳሳይ የእገድ እርምጃ ከወሰዱት መካከል ናቸው
አሜሪካ፤ ቻይና ለስለላ ልትጠቀምበት ትችላለች ያለችውን ቲክቶክ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደምታግድ ቀደም ብላ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ቢዘህም መሰረት ዋይት ሃውስ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በ30 ቀናት ውስጥ በኮምፒውተሮቻቸው እና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቻቸው የቲክቶክ መተግበሪያ እንዲያስወግዱ የሚያስገድድ መመሪያ አውጥቷል፡፡
የአስተዳደር እና የበጀት ጽ / ቤት ዳራሬክተር ሻርኒሳ ያንግ የመንግስት ተቋማት ቲክቶክን በማስወገድ ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ አያያዝ ስርአት እንዲያበጁ ጠይቀዋል፡፡
ዋሽንግተን ተቀባይነቱ እየጨመረ የሄደውን ቲክቶክ አንዱ የብሄራዊ ደህንነት ስጋቷ አድርጋ መመልከት ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡
ቲክቶክን ለማስወገድ በሀገሪቱ ህግ አውጪዎች የቀረበውን ረቂቅ ምክረ-ሃሳብ በሰኔቱ ተቀባይነት ያገኘው ባሳለፍነው ወርሃ ጥር እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ረቂቁ በአሜሪካ ኮንግረስ ጸድቆ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ፊርማ አርፎበት ተፈጻሚ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡
የቻይናው ኩባኒያ ቲክቶክ ይጸደቃል በተባለው ረቂቅ ዙሪያ አስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም፡፡
የፌዴራል ዋና የመረጃ ደህንነት ኦፊሰር ክሪስ ዶሩሀን "ይህ መመሪያ ዲጂታል መሰረተ ልማትዎን ለመጠበቅ እና የአሜሪካን ህዝብ ደህንነት እና የግል ሚስጥርን ለመጠበቅ የወጣና የአስተዳደሩ ቀጣይ ቁርጠኝነት አካል ነው" ብለዋል፡፡
ዋይት ሃውስ፣ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት እና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጨምር በርካታ የፌዴራል ተቋማት ቲክኖተክን መጠቀም ማቆማቸው ተገልጿል፡፡
እንደ አሜሪካ ሁሉ ካናዳ፣ አውሮፓ ህብረት እና ታይዋን በቲክቶክ ላይ ተመሳሳይ የእገድ እርምጃ የወሰዱ ናቸው፡፡
ካናዳ ፤ የሰዎች የግል ደህንነት እና መረጃን የሚያጋልጥና "ተቀባይነት የሌለው ነው" በሚል ቲክቶክን ከመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲወገድ ሰኛ እለት መመሪያ አስተላልፋለች፡፡
ከ50ዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች 19ኙ በከፊልም ቢሆን ቲክቶክን በመንግስት ተቋማት መጠቀም እንደከለከሉ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡
አዲሱ ረቂቅ ህግ ከ130 ሚሊዮን የቲክቶክ ተጠቃሚ አሜሪካውያን ውስጥ 4 ሚሊየን ገደማውን ብቻ የሚያካትት ነው ቢባልም የኩባንያውን ተቀባይነት እንደሚሸረሽረው ባለሙያዎች መናገራቸውን ሮተርስ አስነብቧል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ በቻይናው ኩባኒያ ላይ የተለያዩ ክሶች ቢያቀርቡም ቲክቶክ የሚቀርበው ክስ መሰረተ ቢስ ነው ሲል ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡