አሜሪካውያን የ"ቲክቶክ ስደተኞች" ወደ "ሬድኖት" እየጎረፉ ነው
ቲክቶክ በአሜሪካ ሊዘጋ ነው መባሉን ተከትሎ ሌላኛው የቻይና መተግበሪያ በርካታ ተጠቃሚዎችን እያገኘ ነው ተብሏል
የቲክቶክ ተቀናቃኙ "ሬድኖት" ከ300 ሚሊየን በላይ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች አሉት
ቲክቶክ በአሜሪካ እንዲዘጋ ውሳኔ የሚተላለፍበት ቀን መቃረብን ተከትሎ ሌላኛው የቻይና መተግበሪያ ሬድኖት ተጠቃሚዎች እየበዙለት ነው።
ሬድኖት በቻይና፣ ታይዋን እና በሌሎች ማንደሪን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በሚበዙባቸው ሀገራት የቲክቶክ ተቀናቃኝ ነው።
ራሳቸውን የ"ቲክቶክ ስደተኛ" ብለው የሚጠሩ አሜሪካውያንም ቲክቶክ ከመዘጋቱ በፊት ወደ "ሬድኖት" እየጎረፉ መሆኑን ዴይሊሜል አስነብቧል።
ሬድኖት በትናንትናው እለት በአሜሪካ አፕል ስቶር በአንድ ቀን በብዛት የተጫነ መተግበሪያ ሆኗል።
የቲክቶክ እና ኢንስታግራም ውህድ መሳዩ "ሬድኖት" ከ300 ሚሊየን በላይ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች አሉት።
ተጠቃሚዎቹ በህይወት ዘይቤያቸውን፣ የፍቅር ቀጠሮና ፋሽን ልምዳቸውን ለተከታዮቻቸው የሚያጋሩበት መተግበሪያ ለ"ቲክቶክ ስደተኞች" አማራጭ መዳረሻ ቢሆንም ስጋት መደቀኑ አልቀረም።
መተግበሪያው ቻይና ሰራሽ እንደመሆኑ እንደ ቲክቶክ እና "ሌመን8" ሁሉ የቤጂንግ ባለስልጣናት ለስለላ ሊጠቀሙበት እንደሚችል ሲኤንኤን ባለሙያዎችን አናግሮ ያወጣው ዘገባ አመላክቷል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት በቲክቶክ እጣ ፈንታ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ የያዘው ቀጠሮ አምስት ቀናት ቀርተውታል።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የአሜሪካ ባለስልጣናት ፍርድቤቱ ውሳኔውን ለማሳለፍ የያዘውን ቀጠሮ እንዲያራዝም ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም።
በተያያዘ ቲክቶክ በአሜሪካ እንዳይዘጋ ድርሻውን ለአሜሪካውያን እንዲሸጥ የቀረበለትን ጥያቄ እንደማይቀበለው ያስታወቀ ሲሆን፥ ኤለን መስክ የኩባንያውን ድርሻ ሊገዛ ነው በሚል ብሉምበርግ ያወጣውን ዘገባም "ልቦለድ" ነው ሲል አጣጥሎታል።
በአሜሪካ ከ170 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክቶክ ሊዘጋ ነው መባሉ መልካም ዜና የሆነለት ሬድኖት የተቀናቃኙን "ስደተኞች" እጁን ዘርግቶ እየተቀበለ ነው ተብሏል።
ከ63 ሺህ በላይ ሰዎች "የቲክቶክ ስደተኛ" በሚል ሀሽታግ መልዕክቶችን ያጋሩ ሲሆን፥ ነባር ተጠቃሚዎችም ለአዳዲሶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል እያደረጉ ነው።
አንዳንድ ቻይናውያን የመተግበሪያው ተጠቃሚዎችም "የቻይና ሰላይ" ነን እያሉ በ"ቲክቶክ ስደተኞቹ" ሲሳለቁ መታየታቸው ተዘግቧል።
ታይዋን ሬድኖት የደህንነት ችግር አለበት በሚል የመንግስት ባለስልጣናት መተግበሪያውን እንዳይጠቀሙ ማገዷ ይታወሳል።
ሬድኖት በቻይና "ሺኦሆንግሹ" የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፥ ትርጉሙም ትንሽ ቀይ መጽሃፍ የሚል ነው። ይህም የቻይናውን ኮሚዩኒስት መሪ ማኦ ዜዶንግ መጽሃፍ ይወክላል የሚሉ አካላት ቢኖሩም ሬድኖት ግን ከዚህ ጋር የተያያዘ አይደለም በሚል ያስተባብላል።