በአልጀሪያ መንገደኞችን የሚያቅፈው ቲክቶከር በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ
ግለሰቡ መንገድ ላይ የማያውቃቸውን ሰዎችን የሚያቅፈው ሰላምና አዎንያዊ እሳቤን ለማስፋፋት መሆኑን ገልጾ ይቅርታ ጠይቆ ነበር
በአውሮፓ እየተለመደ የመጣው “መንገደኞችን ማቀፍ” በአልጀሪያ ግን ከባድ ነቀፌታ ገጥሞታል
የአልጀሪያ ፍርድ ቤት በቲክቶክ በርካታ ተከታዮችን ያፈራውን ወጣት በሁለት ወር እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ወሰነ።
ሞሀመድ ራምዚ የተባለው የ30 አመት ወጣት ባለፈው አመት በቲክቶክ የለቀቀው ቪዲዮ ነው ለእስር የዳረገው።
ራምዚ በአውሮፓ ሰዎች በማያውቁት ሰው ለሚቀርብላቸው ሰላምታ ምን ምላሽ ይሰጣሉ በሚል የተጀመረውን የቲክቶክ እንቅስቃሴ በሀገሩ ለመድገም መሞከሩ ነው ለክስ የዳረገው።
ባለፈው አመት በአልጀሪያ ጎዳናዎች የማያውቃቸውን ሰዎች ለማቀፍ ሲሞከር የገጠመውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ማጋራቱን ተከትሎ አልጀሪያውያን ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል አስታውሷል።
ከወግ ባህላችን ያፈነገጠ ድርጊት ነው ያሉ አካላት ክስ አቅርበውበትም በፍርድቤት ነጻ ተብሎ ነበር።
አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆ ለአልጀሪያ የፍትህ ምክርቤት በመቅረቡም ወጣቱ በቅርቡ በሁለት ወራት እስር እና በ37 ሺህ ዶላር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
ራምዚ ከ“መንገደኞችን ማቀፍ” ባሻገር አጫጭር ቀሚስ ያደረጉ፤ አንደኛዋ ንቅሳቷ የሚታይ ሴት የምትታይበት ቪዲዮ ማጋራቱም በክሱ ተካቶበታል።
ወጣቱ ቲክቶከር ቪዲዮዎቹን የሚያጋራው ሰላምና አዎንታዊ እሳቤን ለማስፋፋት በማሰብ መሆኑን በመጥቀስ ይቅርታ ቢጠይቅም ቅጣቱ አልቀረለትም።
በቅጣት ውሳኔው በርካታ አልጀሪያውያን ድጋፋቸውን ቢያሳዩም ሰላምና ፍቅርን መስበኩ ለእስር ሊዳርገው አይገባም በሚል ተቃውሟቸውን የገለጹትም ጥቂቶች አይደሉም ተብሏል።