ሃገራዊ ምርጫው በዚህ ዓመት እንዲካሄድ ተወሰነ
ነሀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ሃገራዊ ምርጫ በወረርሽኙ ምክንያት መራዘሙ የሚታወስ ነው
ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግም ታዟል
ሃገራዊ ምርጫው በዚህ ዓመት እንዲካሄድ ተወሰነ
5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ያካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው ሃገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በተያዘው ዓመት እንዲካሄድ ወስኗል፡፡
ውሳኔውም የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 16/2013 ሆኖ በአንድ ተቃውሞ በ8 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ምክር ቤቱ መስከረም 8 ቀን 2013 ባካሄድው 5ኛ ዙር 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥና ቀጣይ እርምጃዎችን በተመለከተ በጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የቀረበለትን ሪፖርትና ምክር ሃሳብ አድምጦ ነበር፡፡
ሚኒስትሯ በወቅቱ በዓለም ጤና ድርጅት የሚመከሩ የጥንቃቄ መንገዶችን በመተከተል ሃገራዊ ምርጫውን ለማካሄድ እንደሚቻል ምክረ ሃሳብ አቅርበው ነበረ፡፡
ምክረ ሃሳቡን ያደመጠው ምክር ቤቱም በዋናነት ለሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ደግሞ ለህግ፣ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መምራቱም ይታወሳል፡፡
ዛሬም የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባስቀመጡት ምክረ ሀሳብ መሠረት ቫይረሱን በመከላከል ምርጫውን ማከናወን ይቻላል በሚል ከሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበለት የውሳኔ ሃሳብ እና ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ ነው ምርጫው ይካሄድ ሲል የወሰነው፡፡
ሃገራዊ ምርጫው ነሀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲካሄድ ነበር ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት፡፡
ሆኖም በኮሮና ወረርሽኝ እና ምርጫ ቦርድ ማካሄድ እንደማይችል በማስታወቁ ምክንያት ህገመንግስታዊ ትርጉም ተጠይቆበት ወረርሽኙ የህዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ከ9 ወር እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የቀረበለትን የሚኒስትሮች እና የእጩ ዳኞች ሹመት ማጽደቁም አይዘነጋም፡፡