ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት የጋዛን ጦርነት ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተነገረ
የተመራጩ ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ከእስራኤል እና ኳታር መሪዎች ጋር መክረዋል
ዶሃ እስራኤልና ሃማስን ወደማደራደር ሚናዋ ልትመለስ እንደምችትል ተገምቷል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከጥር 20ው በዓለ ሲመታቸው በፊት ለጋዛው ጦርነት መፍትሄ ለመስጠት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተሰምቷል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ የጋዛን የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን መልቀቅ ስምምነት ላይ ለመምከር ወደ ኳታር እና እስራኤል መጓዛቸውን ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
በትራምፕ አስተዳደር የቀጠናው መልዕክተኛነት ስፍራን በይፋ የሚረከቡት ስቲቭ ዊትኮፍ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱራህማን አልታኒ ጋር ተወያይተዋል ነው የተባለው፡፡
የዊትኮፍ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ በባይደን አስተዳደር፣ በኳታር እና ግብጽ አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየውን ያልተሳካ የተኩስ አቁም ድርድር ዘላቂ ተኩስ አቁምን ለማስፈጸም በሚረዳ አዲስ አካሄድ ላይ ለመነጋገር ያለመ ነው፡፡
ውይይቱ ኳታር ባለፈው ወር ከጋዛ አደራዳሪነት ራሷን ማግለሏን ካሳወቀች በኋላ ዳግም ወደ ድርድር ሚናው መመለሷን አመላካች መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ከቀጠናው መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ፕሬዝዳንቱ ስልጣን ከያዙ በኋላ ጋዛን እና አካባቢውን ማረጋጋት ላይ እንዲያተኩሩ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከበዓለ ሲመቱ በፊት እንዲፈጸም ተስማምተዋል፡፡
የባይደን አስተዳዳር የቀጠናው የትራምፕ መልዕክተኛ ከእስራኤል ኳታር እና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር እየተወያዩ እንደሚገኙ እውቅናው እንዳለው ገልጾ፤ ጦርነቱን የሚያስቆሙ እና ታጋቾችን የሚያስመልሱ የትኛውንም አሜሪካ መር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች እደግፋለሁ ብሏል፡፡
ሆኖም ተሰናባቹ እና አዲስ የሚተካው አስተዳደር በተኩስ አቁሙ ዙርያ በጋራ ለመስራት ያሰቡ አይመስሉም ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡
የትራምፕን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በበጎ እንደሚመለከተው ያስታወቀው ሀማስ በበኩሉ በዘመነ ትራምፕ በሚኖሩ የተኩስ አቁም ስምምነት ሂደቶች ዙርያ ለመወያየት በቅርቡ አመራሮቹን ወደ ዶሃ እንደሚልክ አስታውቋል፡፡
ትራምፕ ከሰሞኑ "ታጋቾቹ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆኜ ቢሮ ከምገባበት ከጥር 20 2025 በፊት ካልተለቀቁ በመካከለኛው ምስራቅ ከባድ ችግር ይፈጠራል፤ ይህን ግፍ የፈጸሙትም ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል" ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም "ይህን ግፍ የፈጸሙ በረጅሙ የአሜሪካ ታሪክ ማንም ከተመታው በላይ በከባዱ ይመታሉ" ሲሉ ዝተዋል፡፡
የፍልስጤሙ ሀማስ ታጋቾቹን ለመልቀቅ ከመስማማቱ በፊት ጦርነቱ እንዲቆም እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንዲወጣ ጠይቋል።
ሀማስ በ2023 በእስራኤል ላይ ከባድ ጥቃት በመፈጸም የእስራኤል-አሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸውን ጨምሮ ከ250 በላይ ሰዎችን አግቶ መውሰዱን የእስራኤል መረጃ ያመለክታል።
በጋዛ ተይዘው ከሚገኙት 101 የውጭ እና የእስራኤል ዜጎች ውስጥ ግማሽ ገደማ የሚሆኑት በህይወት አሉ ተብሎ ይታመናል።