“የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ንግስት” ቲና ተርነር በ83 አመቷ ህይወቷ አለፈ
ቲና ተርነር “ዋትስ ላቭ ጋት ቱ ዱ ዊዝ ኢት” እና "ፕራይቬት ድንሰር" በሚሉ ድንቅ ሙዚቃዎቿ ይበልጥ ትታወቃለች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ ታዋቂ ሙዚቀኞችና አድናቂዎቿ ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው
በ1950ዎቹ ወደ ሙዚቃው አለም ተቀላቅላ በሮክ ኤንድ ሮል የሙዚቃ ስልት የነገሰችው ቲና ተርነር በ83 አመቷ ህይወቷ አልፏል።
ቲና ተርነር በስዊዘርላንድ ዙሪክ አቅራቢያ ካስናችት በተባለችው ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ማረፏ ተገልጿል።
“ዋትስ ላቭ ጋት ቱ ዱ ዊዝ ኢት” በሚለው ዜማዋ በመላው አለም ተወዳጅነትን ያተረፈችው ቲና ተርነር፥ በ1950ዎቹ የጀመረው ዝናዋ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው።
በ1980ዎቹ ስድስት ጊዜ የግራሚ ሽልማት የወሰደችው ቲና “ዘ ቤስት”፣ “ታይፒካል ሜል”፣ “ቤተር ቢ ጉድ ቱ ሚ” የሚሉና በተለያየ ጊዜ ምርጥ 40 ውስጥ የተካተቱ ስራዎችን አበርክታለች።
በ1984 የወጣው “ፕራይቬት ዳንሰር” የተሰኘው አልበሟም በቢልቦድር የሙዚቃ ሰንጠረዥ ከፊት መቀመጡን ሬውተርስ ያስታውሳል።
ይህ አልበም ከ200 ሚሊየን በላይ ቅጂው መሸጡንም በመጥቀስ።
“ፕራይቬት ዳንሰር” በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለተለያዩ ድራማዎች ማጀቢያነት መዋሉም በኢትዮጵያውያን ዘንድ በልዩነት ይታወሳል።
በመድረክ አያያዟ የተለየ ተሰጥኦ ያላት ቲና ተርነር በፈረንጆቹ 1988 በሪዮ ዴጄኔሮ ያቀረበችውን የሙዚቃ ኮንሰርቷን ለመታደም 188 ሺህ አድናቂዎቿ ተገኝተዋል።
ይህም ለአንድ ሙዚቀኛ በርካታ ሰዎች የተሰባሰቡበት የሙዚቃ ድግስ ተብሎ ይጠቀሳል።
ቲና ከጊታር ተጫዋች የቀድሞ ባለቤቷ ይደርስባት የነበረውን ጥቃትም በሙዚቃዎቿ አሳይታለች።
በ1985 ከጀርመናዊው ኢርዊን ባች ጋር በመሆን ሁለት አልበሞችን የለቀቀችው ቲና፥ በሙዚቃዎቿ አለምን ዞራለች።
ከባች ጋር ጋብቻ ከፈጸመች በኋላም አሜሪካዊ ዜግነቷን ጥላ ስዊዘርላንዳዊ ሆናለች።
ቲና ተርነር ሙዚቃ መጫወት ካቆመች በኋላ ግን በካንሰርና ሌሎች ህመሞች ትሰቃይ ነበር።
በተለይ ክሬግ የተሰኘው ልጇ በ2018 በ59 አመቱ በሎስ አንጀለስ ራሱን ማጥፋቱና ከአራት አመት በኋላ ታናሹ ሮኒ ህይወቱ ማለፉ የሙዚቃ ንግስቷን ህይወት እንዳመሳቀሉት ይነገራል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ ታዋቂ ሙዚቀኞችና አድናቂዎቿ ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከአርሶአደር ቤተሰብ ወጥታ አለምን ያስደሰተችውን ቲና ብቃት “በክፍለ ዘመን ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ነው” ብለው አሞካሽተዋታል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም “ያላፈችውን እውነት በደስታ እና በሀዘን የዘፈነች” በሚል ገልጸዋታል።
በሙዚቃው አለም ቲና ተርነርን የተከተሉትም በማህበራዊ ሚዲያዎች አድናቆታቸውንና ሀዘናቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።