ውሃ መጠጣት፣ ከመኝታ በፊት ሙቅ ሻወር መውሰድ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ከችግሩ የሚገላግሉ ፍቱን መላ ሆነው ተጠቅሰዋል
ያንኮራፋሉ? እንግዲያውስ እነዚህን መላዎች ይሞክሯቸው።
በአሜሪካ ከ52 በመቶ በላይ ወጣቶች ሲተኙ እንደሚያንኮራፉ አዲስ ጥናት አሳይቷል።
ዋንፖል በ2 ሺህ ወጣቶች ላይ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት የማንኮራፋት ችግር ምን ያህል ስር እየሰደደ መምጣቱን አመላክቷል።
በጥናቱ ውስጥ ከተሳተፉት ወጣቶች ውስጥ 53 በመቶው ወይ ያንኮራፋሉ አልያም ከሚያንኮራፋ ሰው ጋር ይኖራሉ፤ በዚሁ ችግር ከመማረራቸውም የተነሳ ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ይላል ጥናቱ።
ማንኮራፋታቸውን ያስቆማል ላሉት ሁሉ በአመት በአማካይ እስከ 600 ዶላር ለማውጣት የማያቅማሙት በርካታ መሆናቸውን የሚያነሳው ጥናቱ፥ ከ42 በመቶ በላይ በዚህ ችግር ውስጥ ያሉት ሰዎች በቀዶ ህክምና ጭምር ከክፉ አባዜያቸው ለመላቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው አመላክቷል።
ማንኮራፋት እንቅልፍን በመበጥበጥ 38 በመቶ የሚሆኑ ጥንዶችን አልጋቸውን እንዲለያዩ ማድረጉም ጉድ ኒውስ ኔትወርክ ላይ የወጣው ጥናት አሳይቷል።
60 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎችም ችግሩ እንደማይቀረፍ ወደማመኑ መቃረባቸው ተመላክቷል።
ጥናቱ ከማንኮራፋት ችግር ያወጣሉ ተብለው በተሳታፊዎቹ የተመከሩ ነጥቦችንም አካቷል።
ውሃ መጠጣት፣ ከመኝታ በፊት ሙቅ ሻወር መውሰድ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚሉት በበርካቶች እንደ ፍቱን መላ ተጠቅሰዋል።
ከዚህ በታች የተዘረዘሩትም በጥናቱ ተሳታፊዎች የተጠቆሙ መፍትሄዎች ናቸው።
1. ተጨማሪ ትራስ መጠቀም
2. የአይን ጭምብል ማድረግ
3. ከመኝታ በፊት አልኮል አለመጠጣት
4. ሙቅ ሻወር ወስዶ መተኛት
5. ውሃ አብዝቶ መጠጣት
6. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
7. የጸረ ማንኮራፋት መድሃኒቶችን መውሰድ
8. በጎን መተኛት
9. አፍንጫን በቫዝሊን ማሸት
10. ናና መብላት ወይም በሻይ መልክ መጠጣት
የእንቅልፍ ባለሙያዋ ኦሊቪያ አዜዞሎ ግን የጥናቱ ተሳታፊዎች ያቀረቧቸውን ምክሮች መሞከሩ ባይከፋም ቀጣዮቹ አራት መፍትሄዎች በበርካታ ባለሙያዎች የሚመከሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
1. በጎን መተኛት - በጀርባ ተንጋሎ መተኛት የማንኮራፋት ችግርን ያባብሳል። ወደ አልጋ ጠርዝ ጠጋ ብሎ በጎን በኩል መተኛት ግን ችግሩን ለመቀነስ ያግዛል።
2. ክብደትን ማስተካከል - ያልተመጣጠነ የሰውነት ክብደት እና ማንኮራፋት እንደሚያያዙ ጥናቶች አመላክተዋል። ከቀጫጭን ሰዎች ይልቅ ወፍራሞች ለችግሩ ተጋላጭ ናቸውና ክብደትዎን ጤናማ ለማድረግ ይሞክሩ ትላለች ባለሙያዋ።
3. መድሃኒቶችን መውሰድ- አፍንጫን የሚዘጋጉ ነገሮችን የሚከፋፍቱ በፈሳሽ መልክ የሚዘጋጁ መድሃኒቶች አሉ፤ በሃኪም ትዕዛዝ እነዚህን መድሃኒቶች በሚገባ መውሰድም ሌላው መፍትሄ ሆኖ ቀርቧል።
4. ከመኝታ በፊት አልኮል አለመውሰድ - አልኮል መውሰድ የመተንፈሻ ጡንቻዎችን በማዛል ስራቸውን በሚገባ እንዳይከውኑ ያደርጋል፤ ይህም ማንኮራፋትን ያስከትላል የሚሉት የእንቅልፍ ባለሙያዋ ኦሊቪያ አዜዞሎ ከመኝታ በፊት አልኮል መውሰድ እንደማይገባ ያሳስባሉ።